ሕዳር 16/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ አካልነቱ ለጂኦሎጂ ጥናት ተመራጭ በሆነው የአፋር ክልል፣ በመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት የሚፈጠሩ የተፈጥሮ ክስተቶችን ወደ ጂኦ-ቱሪዝም ሀብትነት ለመቀየር የሚያስችል ጥናት ሊካሄድ እንደሆነ የአዋሸ ብሔራዊ ፓርክ አስታውቋል።
ፓርኩ በተለይም ከከርሰ ምድር የሚወጣውን ፍል ውሃ እና እንፋሎት በሳይንሳዊ መንገድ በማጥናት አካባቢውን የምስራቅ አፍሪካ የጂኦ-ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ታቅዷል።
የአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ አቶ አደም መሐመድ፤ "በፓርኩ ሰሜናዊ እና ምዕራባዊ ክፍሎች አልፎ አልፎ የሚከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ለየት ያሉ የፍል ውሃ እና የእንፋሎት ክስተቶችን ይፈጥራል" ሲሉ ለአሐዱ ሬዲዮ ተናግረዋል።

ፓርኩ ይህንን የተፈጥሮ ሀብት ለማልማት የያዘው እቅድ፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ያገናዘበ እንደሆነ ተነስቷል።
የአዋሽ ብሔራዊ ፓርክም ይህንን ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ወደ ሀገር ውስጥ በማምጣት፤ በመሬት መንቀጥቀጥ የሚፈጠሩ ክስተቶች ለጎብኚዎች ያላቸውን መስህብነት በጥናት ለመለየት እና ለማልማት አቅዶ እየሰራ ነው ተብሏል።
በመሬት መንቀጥቀጥ ምክንያት የተፈጠረው አዲሱ የተፈጥሮ ሀብት ለጎብኚዎች ክፍት ከመደረጉ አስቀድሞ፤ አካባቢው በምን መልኩ መልማት እንዳለበት እና የቱሪስቶችን ደህንነት በጠበቀ ሁኔታ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል ዝርዝር ጥናት ማከናወን ወሳኝ በመሆኑ ይህንኑ በእቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ የአዋሽ ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ አቶ አደም መሐመድ አብራርተዋል።
አይስላንድ እና ኒውዚላንድ ንቁ የእሳተ ገሞራ እንቅስቃሴዎችን እና የፍል ውሃዎችን (Blue Lagoon) ከፍተኛ ገቢ ወደሚያስገኝ የቱሪዝም ከቀየሩ ሐገራት መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ