ሕዳር 17/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ከ90 ሚሊዮን ዶላር በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል እዳ ያለባት እና በእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ የምትገኘው ሱዳን፤ በአንድ ዓመት ከ6 ወር እዳዋን ለመክፈል ተስማምታ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ማቋረጧን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለአሐዱ ሬዲዮ ገልጿል፡፡
ወደ ጦርነት ከመግባቷ በፊት ከኢትዮጵያ ጋር የሀይል ሽያጭ ስምምነት የተዋዋለችው ሱዳን ከሁለት ዓመት በላይ ባስቆጠረው ጦርነት እዳዋን መክፈል እንዳልቻለች እና ትወስደው ከነበረው ከ120 ሜጋ ዋት ወደ 10 እና 20 ሜጋ ዋት የኃይል ፍጆታዋ ዝቅ ማለቱ መገለጹ የሚታወስ ነው፡፡

በዚህም በ2017 ዓ.ም አጋማሽ ያለባትን እዳ ለመክፈል ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር የመክፈያ ቀን ድርድር አድርጋ በ1 ዓመት ከ6 ወር እንድታጠናቀቅ የጊዜ ገደብ ቢሰጣትም፤ 1 ሚሊየን ዶላር ብቻ ከፍላ ሂደቱ መቋረጡን የኃይል መስሪያ ቤቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል በሽያጭ ከምታቀርብላቸው የጎረቤት ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ሱዳን እዳዋን መክፈል ባትችልም ሌሎቹ ሀገራት ማለትም ጅቡቲ ኬንያ እና በሙከራ ደረጃ ኃይል እየገዛች ያለችው ታንዛኒያ እዳቸውን በወቅቱ እየከፈሉ የኃይል ሽያጩም እየተከናወነ መሆኑን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከውሃ ኃይል የምታገኘውን 90 ከመቶ በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ለሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለውጭ ማቅረብ ከጀመረች በኋላ ያሉት መሻሻሎች እየጨመሩ ነው ተብሏል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ