ሕዳር 17/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የዘረመል ምሕንድስናን የመሳሰሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከመጠቀም በፊት፤ ባለፉት 20 እና 30 ዓመታት በኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች የቀረቡ የምርምር ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው ወደ ተግባር ሊለወጡ እንደሚገባ አሐዱ ያነጋገራቸው የግብርና ባለሙያዎች አሳስበዋል።

ባለሙያዎቹ ለዘርፉ ውጤታማነት የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች መምጣት ጠቃሚ ቢሆንም፤ ቅድሚያ ግን ያልተነኩ አቅሞችን መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።

የምርትና ምርታማነት ችግሮችን ለመፍታት የተቀመጡ ነባር ጥናቶችን ወደ መሬት ማውረድ እንደሚገባ የገለጹት የግብርና ባለሙያው አቶ ዓለማየሁ ዓሊ፤ "በቅጡ ያልተረዳነውን ከተፈጥሯዊ አካሄድ ያፈነገጠ አዳዲስ ቴክኖሎጂ ከመተግበር ይልቅ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው የኢትዮጵያውያን ተመራማሪዎች ውጤታማ ጥናት ነው" ብለዋል።

በተለይም በእንስሳትና በሰብል ምርታማነት ዙሪያ የተሠሩ ሥራዎች ተግባራዊ ቢደረጉ ዘርፉን በሚጠበቀው ልክ ውጤታማ ማድረግ እንደሚቻልም አስገንዝበዋል።

ሌላኛው በጉዳዩ ላይ ለአሐዱ ሬዲዮ አስተያየታቸውን የሰጡት የግብርና ባለሙያ አቶ ተከተል ዘነበ፤ "በዘረመል ምሕንድስና የተሻሻሉ የሰብልና የእንስሳት ዝርያዎችን መጠቀም ሀገሪቱ በምግብ ሉዓላዊነት ራሷን እንድትችል የማገዝ አቅም ቢኖረውም፤ ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ከዚህ ቀደም ለተሠሩ የግብርና ምርምር ሥራዎች እንደሆነ አብራርተዋል።

Post image

"ከዘረመል ምሕንድስና ጋር በተያያዘ የሚሰነዘሩ አስተያየቶች ቴክኖሎጂውንና ጥቅሙን ካለመረዳት የመነጩ ናቸው" ያሉት ደግሞ፤ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የግብርና ባዮ ቴክኖሎጂ መሪ ተመራማሪ ታደሰ ዳባ (ዶ/ር) ናቸው።

ዶክተር ታደሰ አክለውም፤ በዘረመል ምሕንድስና የሚመረቱ ምርቶች ከ50 ዓመታት በላይ ውጤታማነታቸው በተግባር የተረጋገጠ በመሆኑ "ስጋት ሊኖር አይገባም" ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከማስተዋወቅ ጎን ለጎን ሌሎች ነባር የምርምር ውጤቶችን ተግባራዊ የማድረግ ሥራ እየሠራ መሆኑም ተመላክቷል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ