ሕዳር 25/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በሚቀጥሉት 10 ቀናት ውስጥ በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከዜሮ ዲግሪ ሴንቲግሬድ በታች የሆነ የሙቀት መጠን እንደሚመዘገብ አስታውቋል።
ይህንን ከባድ ቅዝቃዜ ተከትሎ፤ በተለይም በሌሊትና በማለዳ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።
የኢንስቲትዩቱ የሚቲዎሮሎጂ ትንበያ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ (ዶ/ር) ለአሐዱ ሬዲዮ እንዳስታወቁት፤ ከፍተኛ የሆነው የሌሊቱ እና የማለዳው ቅዝቃዜ በሚቀጥሉት 10 ቀናት የሚስተዋል ይሆናል።
ይህ ቅዝቃዜ በኢትዮጵያ ከጥቅምት እስከ ጥር ያለውን ጊዜ በሚያጠቃልለው እና "በጋ" ተብሎ በሚታወቀው ወቅት የሚከሰት የተለመደ የአየር ሁኔታ ቢሆንም፤ የዘንድሮው መጠን ከፍተኛ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ በአብዛኛው አካባቢዎች ማለትም በምስራቅ አማራ፣ በደቡብ ትግራይ፣ እንዲሁም በመካከለኛው የሀገሪቱ ክፍል አዲስ አበባን ጨምሮ ደረቅ፣ ነፋሻማ እና ፀሐያማ የአየር ሁኔታዎች እየተስተዋሉ ነው።
ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥም ቢሆን በአዲስ አበባን ጨምሮ በደብረ ብርሃን፣ በአምባ ማርያም፣ በባቲ እና በደቡብ የሀገሪቱ ክፍሎች፤ የቀኑ ዝቅተኛ የሙቀት መጠን ከ5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በታች ሆኖ መመዝገቡ ተገልጿል። በአዲስ አበባም ከፍተኛ ቅዝቃዜ እየተስተዋለ ነው።
ለዚህ ከፍተኛ ቅዝቃዜ መከሰት ምክንያት የሆነው የአየር ሁኔታ ከሳይቤሪያ በመነሳት ወደ ኢትዮጵያ የሚነፍሰው ደረቅ እና ቀዝቃዛ ነፋስ መሆኑ ተነግሯል።
የአንድ ሀገር የአየር ሁኔታ የሚወሰነው በሀገር ውስጥ ሁኔታዎች ላይ ብቻ ሳይሆን፤ ከከባቢ አየር፣ ከውኃ አካላት እና ከየብስ የሚነሱ ሁኔታዎች ላይ በመመሥረት እንደሆነ ተጠቅሷል።
ኢንስቲትዩቱ ባቀረበው ትንበያ መሠረት፤ በዚህ ወቅት አንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የዝናብ ስርጭት እንደሚኖር ተገልጿል። በተለይም ለደቡብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች 45 ከመቶ የሚሆነውን የሁለተኛ የዝናብ ስርጭት የሚያገኙበት ወቅት እንደሆነ ተጠቁሟል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በሚቀጥሉት ቀናት የሙቀት መጠኑ ከ0 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በታች ሊወርድ እንደሚችል ተገለጸ