ጥቅምት 26/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ታስቦ ላለፉት 2 ዓመታት በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት የተሰጠውን የመምህራን የክረምት ስልጠና ከተሳተፉ 110 ሺሕ የ2ኛ ደረጃ መምህራን መካከል፤ 70 በመቶዎቹ የብቃት ምዘና ፈተናውን ማለፋቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
መምህራኖቹ በማስተማሪያ ይዘት፣ በትምህርት መስክ ዕውቀት፣ በማስተማር ሥነ-ዘዴ እና በዲጂታል ክህሎት ዙሪያ የወሰዱትን የብቃት ማረጋገጫ ፈተና በጥሩ ውጤት ማጠናቀቃቸውን የገለጸው ሚኒስቴሩ፤ 85 በመቶ የሚሆኑ የትምህርት ቤት አመራሮችም በተመሳሳይ ከማለፊያ ነጥቡ በላይ አስመዝግበዋል ብሏል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር አጠቃላይ የትምህርት ልማት ዘርፍ የመምህራን እና የትምህርት ቤት አመራሮች መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሙሉቀን ንጋቱ (ዶ/ር)፤ በተለይ ከ2016 ክረምት ጀምሮ የመምህራን ስልጠና ትኩረት በሚያስተምሩት የትምህርት ዓይነት ላይ ተጨባጭ ብቃት እንዲያዳብሩ ማገዝ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በሥልጠናው መምህራንን ብቻ ሳይሆን የትምህርት ቤት አመራሮችን አቅም እንዲያጎለብቱ ከፍተኛ ትኩረት መሰጠቱን አብራርተዋል።
ይህን የክረምት ስልጠና በመጀመሪያው ዓመት ከ52 ሺሕ በላይ እንዲሁም በሁለተኛው ዓመት ደግሞ ከ62 ሺሕ በላይ መምህራንን በአጠቃላይ ከ110 ሺሕ በላይ መምህራን የወሰዱት ሲሆን፤ አብዛኞቹ መምህራን እና አመራሮች የተሰጣቸውን የብቃት ማረጋገጫ ፈተና በጥሩ ውጤት አጠናቀዋል ተብሏል፡፡
የማለፊያ ነጥብ ያላገኙት 30 በመቶዎቹ መምህራን በቀጣዩ የክረምት የትምህርት ዘመን በድጋሚ ሥልጠናውን ወስደው ለፈተና እንደሚቀመጡ መሪ ሥራ አስፈጻሚው ለአሐዱ አስታውቀዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ