ጥቅምት 26/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ከቻይና ጋር የኢኮኖሚ አጋርነት ስምምነት ለተፈራረሙ የአፍሪካ ሀገራት ምርቶች የዜሮ ታሪፍ ስርዓት ተግባራዊ እንደሚደረግ መግለጻቸውን ተከትሎ፤ ስምምነቱን ከፈረሙ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ በዚህ ስርዓት ውስጥ ተጠቃሚ የምትሆንበትን አሰራር መዘርጋት እንደሚገባት አሐዱ ያነጋገራቸው የዘርፉ ምሁራን ጠቁመዋል።

ሁሌም ቢሆን ታሪፍ መቀነስ የኢኮኖሚን እድገት ለማምጣትና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ጠቃሚ መሆኑን የሚያነሱት፤ የቢዝነስና ኢንቨስትመንት አማካሪው አቶ ከፈለኝ ሀይሉ ናቸው።

በዚህ ስርዓት ግን በርካታ ምርቶችን ኤክስፖርት የምታደርገው ወይም ወደ ኢትዮጵያ የምታስገባው ቻይና ስለሆነች፤ የዜሮ ታሪፍ ስርዓትን ተግባራዊ ስታደርግ ጠቀሜታው ለቻይና የንግድ እንቅስቃሴ እንደሆነ ገልጸዋል።

ነገር ግን ኢትዮጵያም መጠቀም ከቻለች መልካም አጋጣሚ መሆኑን አንስተው፤ ከዚህ ቀደም እንደ የአሜሪካ የአፍሪካ የቀረጥ ነጻ ንግድ ዕድል (አጎዋ) የመሳሰሉትን ለመጠቀም ሙከራ ተደርጎ እንደነበር አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በአጎዋ ውስጥ ረዥም ዓመት የተሰጣት ቢሆንም ሳትጠቀምበት መቆየቷን በመግለጽ፤ ለመጠቀም ስትጀምር ደግሞ መዘጋቱን አስታውሰዋል።

በመሆኑም ቻይና የዜሮ ታሪፍ ስርዓትን ተግባራዊ የምታደርግ ከሆነ ኢትዮጵያ የቻይና ምርቶችን ብቻ ከማስገባት ወይንም (ኢምፖርት) ከማድረግ በዘለለ፤ የወጪ ንግዷን (ኤክስፖርት)ን በማጠናከር የተገኘውን ዕድል ለመጠቀም በቁርጠኝነት መስራት እንደሚጠበቅባት ተናግረዋል።

አሐዱ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ እንዳይላሉ ሰለሞን በበኩላቸው፤ ቻይና የንግድ ሚዛኑን ወደራሷ ለመሳብና ከምዕራባውያን ጋር ያለውን ውድድር ለመወጣት እንደዚህ አይነት ዕድሎችን በማቀድ ልታቀርብ የምትችልበት አግባብ መኖሩን አንስተዋል።

የዜሮ ታሪፍ በዋናነት የኢትዮጵያን ኤክስፖርት እንደሚያበረታታና ተጨማሪ የገበያ አማራጭ ለመጠቀም የሚያስችል ዕድልን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

ከዚህም ሌላ ለሀገር ውስጥ አምራቾች ጠቀሜታ እንዳለው በማንሳት፤ ለሀገሪቱም ጥሩ የገቢ ምንጭ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

ነገር ግን ዜሮ ታሪፍ የሚፈቀደው ለሁሉም ምርቶች ነው ወይስ ደግሞ ለተመረጡት ብቻ የሚለው ጉዳይ ትኩረት የሚሰጥበት እንደሆነ አንስተዋል።

ቻይና ለኢትዮጵያ ዋና የኤክስፖርት መዳረሻ ሳትሆን አብዛኞቹ ምርቶቿን ኢምፖርት የምታደርግባት ሀገር መሆኗን ያነሱት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፤ የዜሮ ታሪፍ ስርዓት ለሁለቱም ሀገራት እኩል ተጠቃሚነትን ሊፈጥር እንደማይችልም ገልጸዋል።

ነገር ግን ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚደረግን የኤክስፖርት ውድድር የተሻለ ሊያደርገው እንደሚችል ያነሱ ሲሆን፤ የዜሮ ታሪፍ ስርዓቱ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ የምትሆንበትን አሰራር መከተል እንደሚገባት ተናግረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ