መስከረም 28/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በሀገር አቀፍ ደረጃ ለአእምሮ ሕመም ከሚጋለጡት ተጎጂዎች መካከል 30 በመቶ የሚሆኑት በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ሆስፒታሎች የሕክምና አገልግሎት እንደሚሰጣቸው ጤና ሚኒስቴር ለአሐዱ አስታውቋል።

በጤና ሚኒስቴር የአእምሮ ጤና ፕሮግራም ባለሙያ የሆኑት አቶ ጀማል ተሾመ ለአሐዱ እንዳስታወቁት ከሆነ፤ እንደ ሀገር 11 በመቶ የሚሆነው ዜጋ በአይምሮ ህመም የተጠቃ ሲሆን ከዚህ ውስጥም ከ30 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሕክምና የሚያገኙት በአዲስ አበባ ነው።

ዜጎች የአእምሮ ሕመም የሚጋጥማቸዉ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ በሆኑ ችግሮች ምክንያት ነው ያሉ ሲሆን፤ ለሕክምናው ወደ ከተማዋ በየጊዜው ከተለያዩ ክልሎች የሚገቡት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

መንግሥት ይህን ችግር ለመቅረፍ፣ ሕክምና የሚሰጡ ተቋማትን በክልሎች ለማስፋት እንዲሁም፤ ሕክምናውን ተግባራዊ አድርገው እንዲሰሩ ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አቶ ጀማል ተናግረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ