መስከረም 28/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ከ50 ዓመታት በፊት በደርግ መንግሥት የተወረሰብኝን ሕንፃ ለማስመለስ በሕግ አግባብ እየጠየቅኩ ነው ሲል የኢትዮጵያ ወጣት ወንዶች ክርስቲያን ማህበር (ወወክማ) ለአሐዱ አስታውቋል።

ማህበሩ የተመሠረተበትን 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል ትናንት መስከረም 27 ቀን 2018 አክብሮ ውሏል።

‎በዚህም ወቅት የወወክማ ቦርድ ፕሬዝዳንት አቶ ኪያ ፀጋዬ ለአሐዱ እንደገለጹት፤ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1949 አራት ኪሎ ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የሚገኘው ዋና መስሪያ ቤት በደርግ መንግሥት የተወረሰ ሲሆን፤ ማህበሩ በተለያየ ጊዜ ሕንጻውን ለማስመለስ ሲሰራ ቆይቷል።

‎ፕሬዝዳንቱ አክለውም፤ ማህበሩ በቀዳማዊ ግርማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ተቋቁሞ በርካታ ሥራዎችን እየሰራ ቆይቶ በደርግ የስልጣን ዘመን ተዘግቶ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

በወቅቱም ሙሉ ንብረቱ ተወርሶ እንደነበር የገለጹ ሲሆን፤ አሁን ላይ በሲቪል ማህበራት ድርጅት በመዝገብ ቁጥር 0511 ዳግም ተመዝግቦ አብዛኛው ንብረቱ ተመልሰውለታል ብለዋል።

‎ነገር ግን የማህበሩ ዋና መሥሪያ ቤት የነበርው ሕንጻ አሁንም ድርስ አልተመለሰለትም፤ በዚም ሙሉ ሰነድ ይዘን ለማስመለስ እየሰራን ነው ብለዋል።

‎ከፌዴራል መንግሥትና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር እንዲሁም፤ ባለድርሻ አካላትን እያነጋገረን ነው፤ የተዘጋጁ ሰነዶችን በማቅረብ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲመለስልን ጥያቄ አቅርበናል ሲሉም አቶ ኪያ ተናግረዋል።‎

Post image


የማህበሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ በፍቃዱ በዛብህ ማህበሩ በአሁኑ ሰዓት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ወጣቶችን በተለያየ የሥራ ዘርፍ ተጠቃሚ ማድረጉ የገለጹ ሲሆን፤ በዚህም በኪነ ጥበብ፣ በፓለቲካ፣ በስፖርት እና መሰል የሥራ ዘርፎች ላይ በርካታ ወጣቶችን ለሀገር ማበርከቱን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ወጣት ወንዶች ክርስቲያን ማህበር (ወወክማ) ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረግ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመስራት 75ኛ ዓመቱን ማስቆጠሩን ገልጸዋል።

ማህበሩ በኢፌዲሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 13/2011 ተመዝግቦ፤ በአዲስ አበባ እና በአምስት ክልሎች በሚገኙ አስር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶቹ የተለያዩ ማህበረሰብ ተኮር ሥራዎች ላይ እያደረገ እንደሚገኝ ተነግሯል።

በአሁኑ ወቅት ከ25 ሺሕ በላይ አባላት ያሉ የኢትዮጵያ ወጣት ወንዶች ክርስቲያን ማህበር (ወወክማ)፤ በ12 ከተሞች ከወጣቶች ጋር የተገናኙ ሥራዎች እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቋል።

‎ወወክማ በዓለም አቀፋዊ ደረጃ በ122 ሀገራት እየሰራ የሚገኝ ማህበር ሲሆን፤ በእንግሊዝ ሀገር ተጀምሮ ወደሌሎች ሀገራት የተስፋፋ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የማህበሩ ዓላማም ሀገር ወዳድ ወጣቶችን ማፍራት፣ ከሱስ ነፃ ወጣት መፍጠር እንዲሁም፤ በአካላዊ፣ መንፈሳዊ እና አእምሯዊ ጠንካራ የሆነ ወጣት ማፍራት የሚሉ ባለሦስት ማዕዘን ምልክቱን መርህ አድርጎ እየሰራ መሆኑ ተመላክቷል።‎

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ