መስከረም 28/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ምግቦች የያዘ ዓለምአቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መዘርዝር (ካታሎግ) ለሕትመት ለማብቃት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስቴር ለሕትመት ለማብቃት በዝግጅት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ባህላዊ ምግቦች መዘርዝር (ካታሎግ)፤ በተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የሚዘወተሩ ባህላዊ ሀገራዊ ምግቦችን አዘገጃጀት፣ ይዘት፣ አቀራረብ እና ታሪካዊ ዳራ ያካተተ ስለመሆኑ ለአሐዱ ገልጿል።
በመጽሐፍ መልክ የሚዘጋጀው መዘርዝር ባህላዊ ምግቦችን እንደ "ብራንድ" ወይም ልዩ የቱሪዝም መገለጫ አድርጎ በማስተዋወቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሏል።

የቱሪዝም ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ዓለማየሁ ጌታቸው ይህ ልማድ በሌሎች ሀገራትም እንዳለ አስታውሰው፤ "ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች መረጃዎችን በማሰባሰብ ጥናት በማካሄድ ላይ ይገኛል" ብለዋል።
ኃላፊው እንዳብራሩት፣ ባህላዊ ምግቦችን መለየትና መመዝገቡ መረጃው በአግባቡ እንዲሰነድ፣ በጊዜ ሂደት እንዳይዘነጋጅ፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኝ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
ባህላዊ ምግቦታቸውን አጥንተው ለጎብኚዎች በሚመች መንገድ ካዘጋጁ ሀገራት መካከል ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ ቻይና፣ ሕንድ እና ኮሪያ ተጠቃሽ ናቸው።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ