ሐምሌ 3/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ለ2018 በጀት ዓመት "የቀዳማይ ልጅነት ዕድገት ልማት ፕሮግራም" ተጠቃሚ ለሆኑ 15 ሺሕ ዜጎች ከ500 ሚልዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን፤ የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ እና የአዲስ አበባ ሕብረት ሥራ ኮሚሽን አስታውቀዋል።
የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ "የቀዳማይ ልጅነት ዕድገት ልማት ፕሮግራም" ቀርፆ ላለፉት 3 ዓመታት በመጀመሪያ ዙር ፕሮግራም ከ20 ሺሕ 250 በላይ ለሚሆኑ እናቶች እና ሕጻናት የአልሚ ምግብ ድጋፍ አድርጓል።
በድጋፉ የተካተቱት ነፍሰጡር ሴቶች፣ የሚያጠቡ እናቶች እና ዕድሜያቸው ከ3 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት ሲሆኑ፤ ቢሮው ለቀጣይ ሦስት ዓመት የሚተገበር 2ኛ ዙር ሥራውን ለመስራት የሚያስችለውን ፕሮግራም በይፋ አስጀምሯል።
የአካል እና የአዕምሮ እድገት የሚዳብረው እስለ 6 ዓመት ባለው ዕድሜ እንደሆነ ያነሱት የቢሮው ኃላፊ ቆንጂት ደበላ፤ በእዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆችን ትኩረት ሰጥቶ መደገፍ የፕሮግራሙ ዓላማ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በዋናነት ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ እናቶች እና ሕጻናት ላይ የሚያተኩረው ፕሮግራሙ፤ በ2014 ዓ.ም. ሲጀመር 7 ሺሕ 866 ተጠቃሚዎችን ይዞ በ40 ሚልዮን ብር በጀት እንደተጀመረም አንስተዋል።
በ2017 ዓ.ም. የተጠቃሚዎች ቁጥር ወደ 11 ሺሕ 900 ሲደርስ፤ ባለፊት 3 ዓመታት በአጠቃላይ 843 ሚልዮን ብር ወጪ መደረጉን ገልጸዋል።
በ2018 በጀት ዓመት ለሚተገበረው ደግሞ 15 ሺሕ የሚደርሱ ዜጎች የተካተቱ ሲሆን፤ "518 ሚሊዮን ብር ተመድቦለታል" ብለዋል።
ለሥራው መሳካት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ትብብር እንዳለበት ያስታወሱት ኃላፊዋ፤ በዋናነት ምግብ አቅራቢዎችን በማስተባበር ከአዲስ አበባ ሕብረት ሥራ ኮሚሽን፣ በጀት በመመደብ የአዲስ አበባ ፋይናንስ ቢሮ እንዲሁም ፕሮግራሙን በማስተባበር የከንቲባ ፅ/ቤት የስትራቴጂክ ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት መሳተፋቸውን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ሕብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ልዕልቲ ግደይ በበኩላቸው፤ አልሚ ምግቦችን ከተለያዩ አምራች አርሶ አደሮችና ኢንዱትሪዎች ጋር በመተባበር በማቅረብ፣ ለእናቶችና ሕጻናት የሚያስፈልጉ ምርቶችን የሚያገኙበት መንገድ እንደሚያመቻች ገልጸዋል።
ለሦስት ዓመታት ያክል ይህንን አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ ወደ 33 የሚጠጉ የሕብረት ሥራ ማኅበራት እንደነበሩ አንስተው፤ አሁን ላይ 55 የሚደርሱ ለቀጣይ ሦስት ዓመታት እንዲያገለግሉ መለየታቸውን አክለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በቂ የሆነና ጥራቱን የጠበቀ ምርት መያዝ የሚችል መጋዘን ያላቸው እንደሆኑ አንስተዋል።
በ2018 በጀት ዓመት ተደራሽነታቸውን ከማብዛት አንፃር የበለጠ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ኮሚሽነሯ አስታውቀዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በመዲናዋ ለቀዳማይ ልጅነት ዕድገት ልማት ፕሮግራም ተጠቃሚ እናቶችና ሕጻናት ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ መመደቡ ተገለጸ
