ሰኔ 26/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1 ነጥብ 93 ትሪሊዮን ብር ሆኖ የቀረበውን የፌዴራል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት በዛሬው ዕለት በሙሉ ድምጽ አፅድቋል።

ምክር ቤቱ ሰኔ 3 ቀን 2017 ዓ.ም ባካሄደው 35ኛ መደበኛ ስብሰባው የፌዴራል መንግሥት የ2018 ረቂቅ በጀት አዋጅ ለዝርዝር እይታ እና ምርምራ መመራቱ የሚታወስ ሲሆን፤ ፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴውም የቀረበውን ረቂቅ በጀት አዋጅ መርምሮ ውሳኔ አሳልፏል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በዛሬው ዕለት የቀረበውን 2018 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 1390/2017 ሆኖ በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል።

በዚህም መሠረት የፌዴራል መንግሥት የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ በጀት 1 ነጥብ 93 ትሪሊየን ብር ሆኖ ጸድቋል፡፡

ከፀደቀው በጀት ውስጥ የመደበኛ ወጪ 1 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ብር ወይም 61 ነጥብ 4 በመቶ፣ ለካፒታል ወጪ 415 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ወይም 21 ነጥብ 6 በመቶ፣ ለብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት 315 ቢሊዮን ብር ወይም 16 ነጥብ 3 በመቶ፣ ለክልሎች ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈፀሚያ 14 ቢሊዮን ብር ወይም 0 ነጥብ 7 በመቶ የበጀት ድርሻ እንደሚይዙ ተገልጿል።

ይህ የ2018 በጀት ከ2017 በጀት አንጻር የ34 ነጥብ 4 በመቶ እድገት ያለው ሲሆን፤ ወጪው የሚሸፈነው ከ80 በመቶ በላይ ከሀገር ውስጥ ገቢ ማለትም፤ አዳዲስ የታክስ ምንጮችን ወደ ገቢ ስርዓቱ በማስገባትና የነበሩትን በማጠናከር ገቢን ለመጨመር እንደሚሰራ ተመላክቷል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ