ጥቅምት 7/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) መንግሥት የካንሰር መድኃኒቶች (ኬሞ ቴራፒ) አቅርቦት ላይ ያለውን ችግር ለማቃለል እና ተደራሽነቱን ለማሳደግ፣ ከጠቅላላው ወጪው 63 በመቶ ያህሉን እየሸፈነ እንደሚገኝ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ይህ የድጎማ ሥርዓት ውድ የሆኑ የካንሰር መድኃኒቶች እጥረት እንዳይኖር ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል።
በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈፃሚ ህይወት ሰለሞን (ዶ/ር) ለአሐዱ እንደገለጹት፤ የኬሞቴራፒ መድኃኒት እጅግ ውድ ከመሆኑ ባሻገር የሚከሰት እጥረትን ለመከላከል መንግሥት ከፍተኛውን ወጪ በመሸፈን አገልግሎቱ በድጎማ እንዲቀርብ የማድረግ ሥራ እየሰራ ይገኛል።

መሪ ሥራ አስፈጻሚዋ አክለውም፤ የካንሰር ሕክምና ሰጪ ማዕከላትን በማስፋት፣ ታካሚዎች በወረፋና መሰል ችግሮች እንዳይጋለጡ ሰፊ ሥራዎች እየተሰሩ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
አንድ ብቻ የነበረውን የጨረር ሕክምና ማዕከላት ቁጥር ወደ 5 ከፍ መደረጉንም ገልጸዋል። እንዲሁም ሁለት ተጨማሪ የካንሰር ጨረር ሕክምና ማዕከላት በሂደት ላይ ሲሆኑ፤ አገልግሎቱን የሚሰጡ ባለሙያዎችን የአቅም ማጎልበት ሥራዎች መሰራታቸውን አስረድተዋል።
ዶክተር ህይወት የካንሰር መድኃኒት አቅርቦትን ከፍ ለማድረግ እና በድጎማ የሚቀርብበትን ሁኔታ በማጠናከር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ሁሉም ዜጋ ለከፋ ችግር ሳይጋለጥ የቅድመ ምርመራ እንዲያደርግ እና ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኝ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ላይ በትኩረት መሰራት እንደሚገባም አመልክተዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ