ጥቅምት 7/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ወደ ሥራ ከገባበት ጊዜ አንስቶ ባሉት 21 ወራት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ጎብኚዎችን በማስተናገድ፤ ከ240 ሚሊዮን ብር በላይ ማስገባቱን አስታውቋል።

የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም በትናንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ከሚገኙ አስጎብኚዎች፣ የአስጎብኚ ድርጅት ባለቤቶች፣ ቱሪዝም ጋዜጠኞች፣ ተፅእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች እንዲሁም የኤቨንት ወይም የኩነት አዘጋጆች ጋር በሙዚየሙ በሚካሄዱ ዝግጅቶች ዙሪያ የውይይት መድረክ አካሂዷል።

Post image

በውይይት በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የዓድዋ ሙዚየም ዋና ዳይሬክተር አቶ ግሩም ግርማ፤ ሙዚየሙ በ2016 ዓ.ም. የካቲት ወር በይፋ ሥራ መጀመሩን አስታውሰዋል።

ሙዚየሙ በርካታ ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ኮንፈረንሶችን ለማዘጋጀት የሚያገልግሉ የስብሰባ አዳራሾች እና የመዝናኛ ማዕከላትን እንዳካተተ ገልጸው፤ ወደ ሥራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት 21 ወራት የጎብኚዎች መዳረሻ በመሆን እያገለገለ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

Post image

በዚህ ጊዜ ውስጥም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሙዚየም ጎብኚዎችንና የኮንፈረንስ ተሳታፊዎችን እንዲሁም የተለያዩ ሰልጣኞችን ማስተናገዱን ተናግረዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም፤ በአዲሱ በጀት ዓመት ሙዚየሙ የበለጠ ተጠናክሮ ሀገራዊ አንድነትን ማስፋት ላይ ይሰራል ብለዋል። ለሥራው ስኬት ከሁነት አዘጋጆች እና ከሌሎው ባለድርሻዎች ጋር በጋራ መስራት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተለያየ መልክ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የኹነት አዘጋጆች በመድረኩ ላይ የዕውቅና ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል።

Post image

ከተሸላሚዎቹ መካከል ፍሉለስ ኤቨንት፣ ዲሲቲ ኤቨንት፣ ዋፋ ማርኬቲንግ፣ ሰላም ኤቨንት፣ ዶቃ ኤቨንት፣ ኢትኤል ኤቨንት፣ መላኬር ኤቨንት፣ ዲጄ ራስ ሚኪ ኤቨኝት፣ ኤክሶዶስ ኤቨንት ይገኙባቸዋል።

‎#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ