መስከረም 29/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ‎የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ በሁለት ዓመት ውስጥ ብቻ ከ70 በላይ የሚሆኑ የጥናትና ምርምር ውጤቶች በዓለም አቀፍ የጥናትና ምርምር ጆርናል ማሳተም እንደቻለ ለአሐዱ አስታውቋል።

‎በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ኮንፍረንስ "የላቀ ጥናትና ምርምር ለተሻለ ጤና ስርዓትና አገልግሎት" በሚል መሪ ቃል መስከረም 29 ቀን 2018 ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ አከናውኗል።

የኮሌጁ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር አንተነህ ምትኩ ለአሐዱ እንደገለፁት፤ እንደ ተቋም በጤና ስርዓቱ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት በጥናትና ምርምሩ የማሻሻያ ሥራዎች እየተሰሩ ነው።

‎ከጥናትና ምርምር ውጤት የመነጨው አንዱ ቴክኖሎጂን ከጤና አገልግሎት ጋር በመጠቀም ከእጅ ንክኪ ነፃ የሆነ ወይም ዲጂታል የሆነ የሕክምና አገልግሎት መስጠት ተችሏል ሲሉ ዶክተር አንተነህ ገልጸዋል።

‎አክለውም፤ እንደ ተቋም ሆስፒታሉ ለሀገር ያበረከተው የጤና ሥርዓት ተግዳሮት ላይ ያተኮረ የሥራ ሂደት ለውጥን ከየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ በመነሳት አሁን ላይ እንደሀገር ከ32 በላይ ሆስፒታሎች እየተገበሩት እንደሚገኝ ተናግረዋል።

‎እንደ ሀገር የታካሚዎችን ደህንነት ማሻሻል ላይ ያተኮረ፤ የጤና ባለሙያዎች አገልግሎትን ጨምሮ "በሙያቸው ምን ያህል እርካታ አገኙ?" የሚል፣ ቴክኖሎጂን በጤና ስርዓቱ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል እና መሰል ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቧል።

‎ባለፉት ጥቂት ዓመታት ማነቆ ሆኖ የቆየውን የጥናትና ምርምር በክፍል ደረጃ እንዲደራጅ ማድረግ መቻሉ የተገለጸም ሲሆን፤ በዚህም ወጥነት ይጎድለው የነበረውን የጥናትና ምርምር ሥራዎች በአንድ ክፍል የሚመሩበትን አሰራር ለመተግበር እንደተቻለ ተገልጿል።

‎የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ሀገር አቀፍ የትኩረት አቅጣጫ የሆኑ የምርምር ሥራዎችን በመውሰድ፤ ለእናቶች፣ አፍላ ወጣቶችና ሕጻናት ጤና እንዲሁም አጠቃላይ የታካሚዎች ደህንነት ላይ ብዙ ሥራዎች ሰርቷል ተብሏል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ