መስከረም 30/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) እንደ ሀገር በ2018 ለማስመዝገብ የታቀደውን ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ከግብ ለማድረስ በቅድሚያ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል ሲሉ አሐዱ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች ገልጸዋል።
6ኛው የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፤ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት በ2017 በጀት ዓመት 8 ነጥብ 8 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን ገልጸው፤ በተያዘው በጀት ዓመት 9 በመቶ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ለማረጋገጥ ይሰራል ማለታቸው አይዘነጋም።
ይህንን ተከትሎም አሐዱ "የታቀደውን ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት እውን ለማድረግ ምን ላይ መስራት ይገባል?" ሲል የምጣኔ ባለሞያዎችን አነጋግሯል።
የተገለጸውን ዕድገት ለማስመዝገብ መንግሥት በዋናነት በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም ማምጣት እንዳለበት ለአሐዱ የተናገሩት የምጣኔ ሐብት ባለሙያው ፋሲል ጥላሁን ናቸው፡፡
የአንድ ሀገር እሴት መገለጫ መገኛው ምጣኔ ሀብታዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ መስተጋብሮች እንደሆኑ የገለጹት ባለሙያው፤ ሀገር ሀገር ሆኖ እንዲቀጥል ሦስቱ ዋና ዋና አምዶች ተጣጥመው እና ተመጋግበው መቀጠላቸው የግድ እና አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የኢኮኖሚ መዛባት ፖለቲካውን በእጅጉ መጫኑን የገለጹም ሲሆን፤ ይህም ፖለቲካው የተረጋጋ እንዳይሆን ከማድረጉ በተጨማሪ ምጣኔ ሀብቱ ተፈጥሯዊ ዑደቱ ተስተጓጉሎ በማህበራዊ ዘርፉ ትርምስ ፈጥሯል ብለዋል።
ስለሆነም ምርትና ምርታማነት ለማረጋገጥ ዜጎች ተንቀሳቅሰውና ሰርተው በራሳቸውና በሀገራቸው ምጣኔ ሀብታት ላይ ለውጥ እንዲያመጡ ሰላም ዋነኛ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግሥት የሚከፈለውን ዋጋ ከፍሎ ሀገሪቷን ወደ ሰላሟ መመለስ አለበት ሲሉ አሳስበዋል። እነዚህ ተግባራት ላይ በቅድሚያ መስራት አለበትም ነው ያሉት።
አሐዱ ያነጋገራቸው ሌላኛው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ መልካም ማዳ ቀደም ሲል የቀረበውን ሀሳብ የሚጋሩ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት መሠረት ለሆነው የግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ግብርናው የሀገሪቱን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ፣ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት እና የሌሎች ልማት ሥራዎች ደጋፊ በመሆን እንዲያገለግል መስራት ዕቅዱን ከግብ ለማድረስ ያስችላል ሲሉም ጠቁመዋል።
ሀገሪቱ ላቀደችሁ የኢኮኖሚ እድገት ግብርናው የአምበሳውን ድርሻ ይወስዳል ያሉም ሲሆን፤ ግብርናው እየጨመረ የሚመጣውን የሕዝብ ብዛት ከመመገብ እና የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ ከመሆን በተጨማሪ በቀጣይ ኢኮኖሚውን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር እየተከናወነ ባለው ተግባር አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚገባ አብራርተዋል።
በዚህም መንግሥት ይህን ኃላፊነቱን እንዲወጣ ብዙ መስራት ይጠበቅበታል ባይ ናቸው።
መንግሥት ይህን በመገንዘብ ዘርፉን ማዘመን ላይ በትኩረት በመስራት የታቀደውን 9 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ማምጣት ይቻላል ብለዋል።
ምጣኔ ሀብት ሀገር እንደሀገር መንግሥት እንደመንግሥት እንዲቀጥል ያለው ሚና የጎላ ከመሆኑ አንፃር፤ መንግሥት ሥራዎችን በመስራት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደሚጠበቅበትም ባለሙያዎቹ ገልጸዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በበጀት ዓመቱ የታቀደውን ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ከግብ ለማድረስ በቅድሚያ ሰላምን ማረጋገጥ ይገባል ተባለ
