መስከረም 22/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ተማሪዎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርሲቲዎች) በነበራቸው ቆይታ ሲገለገሉበት የቆዩትን የወጪ መጋራት ክፍያን በተመለከተ፤ ተቀጣሪ ከሆኑ በኋላ አሰሪዎቻቸው ወይም ቀጣሪዎቻቸው ክፍያውን እየፈጸሙ ስለመሆኑ ማረጋገጥ እንደሚገባቸው የገቢዎች ሚኒስቴር ለአሐዱ አስታውቋል።
በዩኒቨርሲቲ የወጪ መጋራት ተጠቃሚ የሆኑ ተማሪዎች ክፍያውን የሚፈፅሙት ሥራ ላይ ሲሰማሩ እንደሆነ የገለጹት፤ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የታክስ ከፋዮች ምዝገባ እና አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ደረጄ ፋና ናቸው።
ትምህርት ሚኒስቴር የወጪ መጋራቱን መጠን መረጃ ለገቢዎች ሚኒስቴር እንደሚሰጥ ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ ሥራ ከተቀጠሩ በኋላ ደግሞ ቀጣሪያቸው ክፍያውን ተግባራዊ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት የወጪ መጋራት ተጠቃሚ የሆኑ እና ወደ ሥራ ዓለም የተቀላቀሉ ሠራተኞች፤ አሁን ላይ ቀጣሪዎቻቸው ክፍያውን እየፈጸሙ ስለመሆኑ ማረጋገጥ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
በግላቸው የሚከፍሉ ካሉም ደግሞ ወደ ገቢዎች ቢሮ በመሄድ ክፍያቸውን በመፈጸም፤ የዜግነት ግዴታቸውን መወጣት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የወጪ መጋራት አዋጁ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ እንደሚገኝ ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ ከዚህ ቀደም ይህንን ተቀናጅቶ ከማስፈፀም አንፃር የነበሩ ክፍተቶችን ለማስተካከል በስፋት እየተሰራበት እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በመሆኑም ከሠራተኞች በተጨማሪ ቀጣሪዎችም በሕግ የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ለማድረግ እንደሚሰራበት አክለዋል።
የገቢዎች ሚኒስቴር በቅርቡ የወጪ መጋራት የአከፋፈል ሂደትን ለማሻሻል ተማሪዎች ተመርቀው ወጥተው ሥራ ከማግኘታቸው አስቀድሞ ገና ወደ ዩኒቨርስቲ ሲገቡ፤ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር እንዲይዙ የሚያድረግ አሰራርን ተግባራዊ ማድረጉ ይታወሳል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የወጪ መጋራት ተጠቃሚ የነበሩ ሠራተኞች ቀጣሪዎቻቸው ክፍያውን እየፈጸሙ ስለመሆኑ ማረጋገጥ እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ
