ጥቅምት 12/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በትግራይ ክልል ከሚገኙ አጠቃላይ የጤና ተቋማት ውስጥ 89 በመቶ የሚሆኑት በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑ በጥናት ተረጋግጧል ሲል የክልሉ ጤና ቢሮ ለአሐዱ ገልጿል፡፡

ከእነዚህ የጤና ተቋማት መካከል 3 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ሙሉ በሙሉ በጦርነቱ የወደሙ መሆናቸውን፤ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አማኑኤል ሃይለ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ጉዳት የደረሰባቸው ተቋማትም ከጤና ኬላ ጀምሮ እስከ ትላልቅ ሆስፒታሎች ድረስ ናቸው ያሉት ኃላፊው፤ ከእነዚህ መካከል 86 በመቶው መካከለኛ ጉዳት የደረሰባቸው መሆናቸውን የተደረገው ጥናት አመላክቷል ብለዋል።

ጥናቱን በጋራ ያጠኑት የዓለም ጤና ድርጅት፣ የኢፌድሪ ጤና ቢሮና የክልሉ ጤና ቢሮ ሲሆኑ፤ ጥናት የተደረገውም የጤናማ የሃብት አገልግሎት አቅርቦት ቁጥጥር ስርዓት (Health Resource And Service Availability Monitoring System) በሚል መሆኑን የቢሮዉ ኃላፊ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በጦርነቱ በክልሉ ይገኙ የነበሩ የሕክምና መገልገያ መሳሪዎች ደግሞ 99 በመቶ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ 72 በመቶ የሚሆኑት መጠነኛ ጉዳት ሲደርስባቸው፣ 27 በመቶ የሚሆኑት የሕክምና መሳሪያዎች ደግሞ ሙሉ በሙሉ በጦርነቱ ወድመው አገልግሎት የማይሰጡ ሆነዋል ብለዋል።

በዚህም በክልሉ የሚገኙ ነፍሰጡር እናቶች፣ ሕጻናትና ሴቶች እንዲሁም ማንኛውም ሰው በቀላሉ የሕክምና አገልግሎት እንዳያገኝ እንቅፋት ሆኗል ሲሉ ኃላፊው ተናግረዋል።

"በክልሉ ከጦርነቱ በፊት የነበረውን የጤናውን ዘርፍ ለመገንባት ከ30 ዓመት በላይ ፈጅቷል" ያሉት ዶክተር አማኑኤል፤ አብዛኞቹ ተቋማት በጦርነት በመውደማቸው ወደ ነበሩበት ለመመለስ አዳጋች መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም "በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ የሚገኙ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በክልሉ በጦርነት የወደመውን የጤና ተቋማት ሙሉ በሙሉ መልሶ በመጠገን፤ የዜጎችን ሕይወት ለመታደግ ድጋፍ እንሻለን" ሲሉ የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አማኑኤል ሃይለ (ዶ/ር) ጥሪ አቅርበዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ