ጥቅምት 12/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በአሰላ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ በሀገር መከላከያ ሠራዊት አባልነት ያገለገሉ ተሰናባች የቀድሞ ሠራዊት አባላት፤ በ2015 ዓ.ም. የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እንደሚሰጠን የተገባልን ቃል እስከ አሁን አልተፈጸመም ሲሉ ለአሐዱ ቅሬታ አቅርበዋል።

ከሠራዊት አባልነታቸው የተገለሉት የአካል ጉዳት ስለደረሰባቸው እንደሆነ የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ቃል የተገባላቸው እንዲፈጸም ተደራጅተው ቢጠብቁም ምላሽ አለማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ጉዳት የደረሰባቸው የቀድሞ የመከላከያ አባላት ባሰሙት ቅሬታ ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም 'እሺ፣ ጠብቁ' ከሚል ምላሽ ውጭ በቂ መረጃም ሆነ የቦታ ድልድል ማግኘት አለመቻላቸውን ተናግረዋል።

አሐዱ የቅሬታ አቅራቢዎችን ጥያቄ በመያዝ የአሰላ ከተማ መሬት አስተዳደር ጽፈት ቤትን ጠይቋል።

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አበበ ረታ፤ "መረጃቸው ተሟልቶ ወደ መሬት አስተዳደር ቢሮ የመጣ ተጎጂዎች ሁሉ በቅደም ተከተል ተስተናግደዋል" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

በ2016 ዓ.ም. ብቻ በ140 ማኅበራት የተደራጁ ከ3 ሺሕ በላይ ሰዎች የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ መሰጠቱን የተናገሩት ኃላፊው፤ የተጎዱት የሠራዊት አባላት ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁንም ተደራጅተው የሚጠብቁ የቀድሞ የመከላከያ አባላት በቅደም ተከተላቸው መሠረት እንደሚስተናገዱ ገልጸው፤ በከተማ ልማት በኩል ተደራጅተው ሙሉ መረጃቸው ወደ መሬት አስተዳደር የመጣ ፋይሎች በሙሉ ተስተናግደዋል ብለዋል።

በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩ እያዘጋጀው የሚገኘው አዲስ የከተማ ፕላን ጸድቆ ሥራ ላይ ሲውል፤ የመኖሪያ ቦታ መሬት ጥያቄዎች ሙሉ ለሙሉ ይፈታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ኃላፊው አቶ አበበ ተናግረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ