መስከረም 29/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) 6ኛው ሀገራዊ የአፍላ ወጣቶች የጤና ፎረም "አንድነት ለተግባራዊ እርምጃ፣ የአፍላ ወጣትነት እርግዝናን ለማስቆም እንተባበር!" በሚል መሪ ቃል በዛሬው ዕለት በሐምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል ተካሂዷል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ደረጀ ዱጉማ፤ 6ተኛውን የአፍላ ወጣቶች ፎረም በሐምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል ማክበር ያስፈለገው አፍላ ወጣቶች ለእርግዝና በሚጋለጡበት ወቅት ለፌስቱላ የሚጋለጡ በመሆናቸው ነው ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

Post image

የአፍላ ወጣቶች እርግዝናን እና ያለ እድሜ ጋብቻን ከኢትዮጵያ ማጥፍት ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ይህን እውን ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ወጣቶች እና አፍላ ወጣቶች ላይ የሚደረግ እንክብካቤ ወደፊት ሀገር የሚረከቡት ዜጎች ላይ መስራት መሆኑን አንስተው፤ በተለይ ሴት አፍላ ወጤቶችን መደገፍ ለሀገር ብልፅግና ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አስታውቀዋል።

አፍላ ወጣቶች ለተለያዩ ችግሮች እንደሚያጋጥሟቸው የገለጹም ሲሆን፤ ወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ችግር፣ ተላላፊ ለሆኑ በሽታ ተጋላጭ የሚሆኑበት ሁኔታ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም ግጭት ባለበት አካባቢ የሚገኙ የአፍላ ወጣቶች ከፍተኛ የሆነ ችግር እንደሚያጋጥማቸው አስታውሰው፤ በሀገሪቱ ከ40 በመቶ በላይ የሚሆኑት ዜጎች ከ20 ዓመት በታች ወደ ጋብቻ ለመግባት የሚገደዱበት እድል ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

አክለውም ወጣቶች እና አፍላ ወጣቶች በዘመን አመጣሽ ሱስ ውስጥ የሚገቡበት እድል ከፍተኛ በመሆኑ፤ ወጣቶች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ጤና ሚኒስቴር አፍላ ወጣቶች ትኩረት በማድረግ የ5 ዓመት እቅድ በማውጣት ከሚተገብራቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት ውስጥ አንዱ፤ ሀገር አቀፍ የአፍላ ወጣቶችና የወጣቶች ጤና ትግበራን በሀገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት ሰጥቶ መስራት መሆኑ ተገልጿል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ