መስከረም 29/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በቀን በአማካኝ ሁለት ኪሎ ግራም ቆሻሻ እንደሚያመነጭ የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ለአሐዱ አስታውቋል።

ይህ መሆኑ ሀገሪቱ ከቆሻሻ መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል የምታገኘውን ገቢ እያሳጣ እና ለበሽታ መባባስ መንስኤ እየሆነ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ለሊሴ ነሜ (ኢ/ር)፤ "የሚጣለው የቆሻሻ መጠን የሚያሳየው ማኅብረተሰቡ ቆሻሻን መልሶ የመጠቀም ግንዛቤው አነስተኛ መሆኑን ነው" ብለዋል፡፡

Post image

ባስልጣኑ ችግሩን ለማቃለል በዋነኛነት እየሰራ ያለው፣ ሕብረተሰቡ የሚያስወግዳቸውን ደረቅ ቆሻሻዎች በመለየት መልሶ የመጠቀም ልምዱን እንዲያሳድግ የግንዛቤ ሥራዎችን በመስራት ላይ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም፤ በተለያዩ የውጭ ሀገራት በጥቃቅንና አነስተኛ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው በቆሻሻ መልሶ መጠቀም ሥራ ላይ እንዲሰማሩ ለማስቻል የሕግ ማዕቀፍ በመዘርጋት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

ኢንጂነር ለሊሴ ሁሉም የሚወገዱ ቆሻሻዎች መልሶ መጠቀም የሚቻሉ ባለመሆኑ ጉዳት የሚያስከትሉትን እና የማያስከትሉትን በጥንቃቄ ለይቶ ኬሚካል ነክ ቆሻሻዎችን በተገቢው መንገድ ማስወገድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ሕብረተሰቡ የሚጥለውን ቆሻሻ መጠን እንዲቀንስ ወይም በአንድ ቦታ በማከማቸት ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚጠበቅበትም ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ