በአዲሱ ሰሌዳ ላይ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እንደማይኖር የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ምክንያቱን ሲገልፅም፤ ሀገሪቱ የሀገራዊ ምክክር እያደረገች በመሆኑ የሰንደቅ ዓላማ ቅርፅ ላይ ለውጥ ሊፈጠር ይችላል በሚል እሳቤ መሆኑን አብራርቷል፡፡
በተጨማሪም በአዲሱ ሰሌዳ ላይ የክልል ስያሜ እንደማይኖርም የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ገልጿል፡፡
'አዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ላይ የሚታተመው የክልል ስያሜ ቀረ' ማለት 'ክልሎች ከተሽከርካሪዎቹ ያገኙት የነበረው የአገልግሎት ገቢ ይቀራል' ማለት እንዳልሆነ፤ የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚነመስቴር ሚኒስትር ዶክተርዓለሙ ስሜ አስረድተዋል፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ከሆነ 'ተግባራዊ ይደረጋል' የተባለው ሰሌዳ ከተሽከርካሪው ላይ መፈታት እንዳይችል ሆኖ የሚመረት ነው፡፡
ይህም የአንዱን መኪና ታርጋ አንዱ መኪና ላይ መለጠፍ እንዳይቻል ያደርጋል ሲሉም የገለጹ ሲሆን፤ ከታርጋው በተጨማሪ መስታወት ላይ የሚለጠፍ ስቲከር መኖሩንም አንስተዋል፡፡
በትላንትናው ዕለት አዲሱን ታርጋ በሚመለከት መግለጫ የተሰጠ ሲሆን፤ ከሁለት ወራት በኃላ ወደ ትግበራ ይገባልም ተብሏል።
ሰሌዳው ሲዘጋጅ ቀደመው የወጡ ምስሎች የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አብሮት እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስትሩ፤ አሁን ላይ ግን እንዲቀር ተደርጓል ብለዋል።
ምክንያቱንም ሲያስረዱ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አንዱ አጀንዳ የሰንደቅ ዓላማ ቅርፅ ይቀየር የሚል በመሆኑ ምናልባት ለውጥ ቢኖር ለረጅም ግዜ ታስቦ የተሰራውን ሰሌዳ እንዳይቀይረው በማሰብ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በኢህአዴግ ዘመን ለአገልግሎት የበቃው እና እስካሁንም በሥራ ላይ ያለው የተሽከርካሪዎች መለያ ቁጥር ሠሌዳ 'ኢት' የሚል መለያ ካላቸው ከተወሰኑ ተሽከርካሪዎች ውጪ አብዛኞቹ የሚንቀሳቀሱባቸውን ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ሥም ሁለት ፊደላትን የያዙ ናቸው።
ይሁን እንጂ በዚህ ዓመት ሙሉለሙሉ ይቀየራል የተባለዉ አዲሱ መመሪያ በአሁኑ ሰዓት በሥራ ላይ ያሉ የተሽከርካሪ ሰሌዳዎች ላይ የሚቀመጠውን የተለያዩ ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች መለያዎችን አላካተተም።
በመላው ኢትዮጵያ አገልግሎት ላይ የሚውሉት የሠሌዳ ቁጥሮችም ተመሳሳይ መለያ እንዲኖራቸው ይደረጋል ተብሏል።
ሁሉም የተሽከርካሪ መለያ ቁጥር ሠሌዳዎች በእንግሊዝኛ እና በግዕዝ ፊደላት ኢትዮጵያን የሚያመለክት አጭር ጽሁፍ እና የኢትዮጵያ ካርታ እንደሚኖራቸዉም የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ሚኒስቴር ገልጿል።
በሀገሪቱ የሚመዘገቡ ሁሉም ተሸከርካሪዎች የሚለጥፉት የመለያ ቁጥር ሠሌዳ ላይ የኢትዮጵያ ካርታ እና ኢትዮጵያ ባፀደቀችው ዓለም አቀፍ ስምምነት መሠረት የተሰጣትን ሀገራዊ ልዩ ምልክት በላቲን "ETH" እንዲሁም በግዕዝ "ኢት" የሚል የግእዝ ፊደላት እና የላቲን ፊደላት ይዘት እንዲኖረው ይደረጋል ተብሏል፡፡
የትራንስፖርትና ሎጅስቲክ የሚኒስቴሩ አለሙ ስሜ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ በሀገሪቱ ያሉ ችግሮች ምክንያት ተሽከርካሪ ላይ በሚደረግ የክልል ስያሜ እንግልት እና አድሎ ሲፈፀም ቆይቷል።
ይህንን የክልል ስያሜን ተሽከርካሪ ላይ እንዲቀመጥ ያደረገው በወቅቱ ስልጣን ላይ የነበረዉ መንግሥት ኢህአዴግ በዋናነት የመለያ ቴክኖሎጂዎች ባለመኖራቸው የክልል ስያሜ ለመጠቀም ተገዶ እንደነበር ተናግረዋል።
የሰሌዳ ቅያሪው በዜጎች ላይ የሚደርስን አድሎ እና ጎቦ ለማስቀረት ያሰበ ቅያሪ ባይሆንም፤ ግን እግረ መንገዱን ችግሩን ይቀርፋል ሲሉም ሚኒስቴሩ ተናግረዋል፡፡
በፊትም አሁንም ማወቅ የሚገባው እና ማወቅ ያለበት አካል ታርጋውን መለየት የሚያስችለው አሰራር ተዘርግቶለታልም ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የነበረው የተሽከርካሪ መለያ ቁጥር ሰሌዳ አመራረትና አሰረጫጨት የአሰራር ክፍተት እና የሃብት ብክነት ይስተዋልበት ነበርም ተብሏል፡፡
ሌላው በትላንትናው ዕለት መግለጫ ላይ ሚኒስተሩ በኢትዮጵያ በግምት 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ተሽከርካሪ ይኖራል ተብሎ እንደሚታሰብ ገልጸዋል።
ነገር ግን "እርግጠኛ መሆን ስለምን አይቻልም?" ተብሎው ከመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጥያቄ የቀረበላቸው ሚኒስቴሩ፤ "ምክንያቶቹ በርካታ ናቸው" ይላሉ፡፡
የመጀመሪያው በኮንትሮባንድ የሚገቡ ተሸከርካሪዎች በርካታ በመሆናቸው ነው ያሉም ሲሆን፤ ከሞተ ወይም አገልግሎት ከማይሰጥ ተሸከርካሪ ላይ ሰሌዳውን እና ፋይሉ ስለሚወስድ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ተመሳሳይ ታርጋ በማሰራት ለተለያየ የሕገ-ወጥ ተግባር የሚሰማሩ አካት በመኖራቸው ቁጥሩን በእርግጠኝነት መናገር አልተቻለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ሚኒስቴር ለዚህ የታርጋ ለውጥ ምን ያህል ወጪ እንደወጣበት የተጠየቀ ቢሆንም፤ ሚኒስትሩ አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ከመናገር ተቆጥበዋል።
በተጨማሪም የታርጋ ለውጡን አስመልክቶ ወጪውን የተሽከርካሪዉ ባለቤት እራሱ እንደሚሸፍንም በትላትናው መግለጫው ወቅት ተነስቷል።
በመድረኩ ሌላው መግለጫ የሰጡት የትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ሚንስትር ድኤታው ዶ/ር በርሆ ሀሰን ናቸዉ፡፡
ሚንስትር ድኤታዉ ቅየራው ሲጀመርም ሁሉም ተሸከርካሪዎች አዲስ የሆነ የታርጋ ቁጥር እንደሚወስዱም የገለፁ ሲሆን፤ የአገልግሎት ክፍያውንም ባለቤቶቹ እንዲከፍሉ ይደረጋል ብለዋል፡፡
አዲሱ የሰሌዳ ቁጥር ኢትዮጵያን የሚገልጹ መለያዎችን የያዘ እንዲሁም ዓለም ዓቀፍ መስፈርቱን የተከተለ ሲሆን፤ 50 ሺሕ ታርጋዎችም በማሳያነት ተዘጋጅተዋል ተብሏል፡፡
የዲጂታል ሥራው ተጠናቅቆ የቅየራ ሒደቱ በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባ የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ በ2018 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ቀይሮ ለመጨረስ ዝግጅት መደረጉን አጽንኦት ሰጥተዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ