ሕዳር 26/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ከአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ወረዳዎች በምግብ ሙያ፣ በቤት አያያዝ፣ በፀጉር ሙያን ጨምሮ የአጭር ጊዜ ስልጠና ለመውሰድ 250 ሰልጣኞች በንፋስ ስልክ ፓሊቴክኒክ ኮሌጅ ስልጠና መውሰዳቸውና የትራንስፓርት እንደሚታሰብላቸው ቃል እንደተገባላቸው ለአሐዱ ገልጸዋል።

በሐምሌ 2017 ዓ.ም ትምህርቱን መጀመራቸውን የገለጹት ሰልጣኞቹ፤ አሁን ስልጠናውን መጨረሳቸውና የተገባላቸው የትራንፓርት አበል እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ ሲጠይቁ መቆየታቸውን አንስተዋል።

በዚህም ቅሬታቸውን ለተለያዩ ተቋማት ማስገባታቸው የገለጹት ሰልጣኞቹ፤ ከቀናት በፊት እያንዳንዳቸው 2 ሺሕ 40 ብር መቀበላቸው ጠቁመው "ነገር ግን የሚደርሰን ይህ አይደለም" ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

ስለሆነም "የንፋስ ስልክ ፓሊቴክኒክ ኮሌጅ ባርሴሎ ፋውንዴሽን ከተሰኘው ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር ያደረገውን ውል ያሳየን" ሲሉ ጠይቀዋል።

አሐዱ በጤና፣ በትምህርት፣ በግብርና ሌሎች መስኮች ድጋፍ የሚያደርገውና የሰልጣኞቹ የትምህርት መሳሪያ አቅርቦትና ሌሎችን ድጋፎች ያደረገውን ባርሴሎ ፋውንዴሽንን ስለጉዳዩ ጠይቋል።

የፋውንዴሽኑ ተወካይ አንዳርጋቸው በቀለ "ተማሪዎቹ በቅድሚያ ሲጀምሩ ስልጠናውን ብቻ እንደነበር እንጂ ቃል አልተገባም ነበር" ያሉ ሲሆን፤ ነሐሴ 30 ቀን 2017 ዓ.ም መጠኑ ያልተገለጸ ነገር ግን የተወሰነ ክፍያ እንደሚኖራቸው ተነግሯቸዋል ብለዋል።

በዚህም ለንፋስ ስልክ ፓሊቴክኒክ ኮሌጅ ብር መግባቱን እና ክፍያው መፈጸሙን ገልጸዋል።

የንፋስ ስልክ ፓሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ሸለመው ንጉሡ በበኩላቸው፤ ስልጠናውን ኮሌጁ እንዲሰጥ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ፋውንዴሽኑ እንዲደግፍ ስምምነት መደረጉን ገልጸዋል።

"ኮሌጁ የመንግሥት በመሆኑ መክፈል የማይችል ነው" ያሉት ዲኑ፤ "ሰልጣኞቹ የትራንስፖርት አበል እንዲከፈላቸው ባርሴሎ ፋውንዴሽንን በመጠየቃቸው 500 ሺሕ ብር በጀት ተለቆ ለእያንዳንዳቸው 2 ሺሕ 40 ብር የትራንስፖርት አበል ተሰጥቷቸዋል" ብለዋል።

አክለውም ከሰልጣኞቹ አስቀድሞ ከስደት ተመላሽ ለሆኑ ሰልጣኞች ስልጠና መሰጠቱና ለእነዚሁ ሰልጣኞች በዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅት (ILO) የመደበላቸው በጀት በመኖሩ፤ "እሱን ማግኘታቸው ለአሁኖቹ ሰልጣኞች የተሳሳተ መረጃና ግንዛቤን ፈጥሯል" ሲሉም ተናግረዋል።

ኮሌጁ በበኩሉ ከባርሴሎ ፋውንዴሽን ጋር ያደረገውን ስምነት ማሳየት የሚችል መሆኑን ከራሱ ከፋውንዴሽኑ ጋር በጋራ መነጋገር እንደሚቻል ገልጸዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ