ሕዳር 25/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባው ሦስት የተለያዩ ሹመቶችን መርምሮ አጸድቋል።
ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎ የሰላም ሚኒስትር፣ የግብርና ሚኒስትር እና የኢቢሲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሹመቶችን አፅድቋል።
ምክር ቤቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተሾሙትን የሰላም ሚኒስትር መሀመድ ኢድሪስ እንዲሁም የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ሹመትን አፅድቋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተመደቡት አቶ ቢንያም ኤሮ ሹመት በምክር ቤት ፀድቋል። ተሿሚዎችም በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው ቃለ መሃላ ፈፅመዋል።
በተጨማሪም ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው የተለያዩ የብድር ስምምነቶችን አጽድቋል።
በዚህም የኢትዮጵያ ምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን አወጅ ቁጥር 1397/2018 በማድረግ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።
በተመሳሳይም በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ የፐብሊክ በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለዘላቂና ንጹህ ኢነርጂ ተደራሽነት ለውጥን ለማፋጠን ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የተደረገውን የ294 ሚሊየን ዶላር የብድር ስምምነት ረቂቅ አዋጅ አዋጅ ቁጥር 1398/2018 በማድረግ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚንስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) የብድር ስምምነቱን አስፈላጊነት ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት፤ 294 ሚሊየን ዶላሩ ስድስት ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ31 ዓመታት ውስጥ የሚከፈል መሆኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ የፐብሊክ በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለምስራቅ አፍሪካ የክህሎት ትራንስፎርሜሽን እና ቀጠናዊ ውህደት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል ተጨማሪ የብድር ስምምነትን ረቂቅ አዋጅ አዋጅ ቁጥር 1399/ 2018 አድርጎ በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የመንግሥት ተጠሪ ሚንስትሩ ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር የተገኘውን የ20ሚሊየን ዶላር ብድር ከወለድ ነጻ መሆኑን ገልጸው ፤ የስድስት ዓመታት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 ዓመታት ውስጥ የሚከፈል መሆኑን ለምክር ቤቱ አብራርተዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ