ሕዳር 26/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ በዓመት ከ1 ሺሕ 500 እስከ 2 ሺሕ የሚደርሱ መዝገቦች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ እንደሚሰጥ የአጣሪ ጉባኤው አባላትና የሕግ ባለሙያዎች ለአሐዱ ሬዲዮ አስታውቀዋል።

የተለያዩ ሀገራት የሕገ-መንግሥት ትርጉምን በሚመለከት የተለያየ ልምድ እንዳላቸው የገለጹት የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አባልና የሕግ ባለሙያው ምትኩ ማዳ፤ አንዳንዶቹ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮችን ብቻ የሚያዩ ሕገ-መንግሥታዊ ፍ/ቤት እንዳላቸው አንስተዋል።

በሌላ በኩል በሀገራቱ ጠቅላይ ፍ/ቤት አማካኝነት ሕገ-መንግሥቱን የመተርጎም ልምድ ያላቸው ሀገራት እንዳሉ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ደግሞ የሕገ-መንግሥት ትርጉምን በሚመለከት ኃላፊነትና ስልጣን የተሰጠው ለፌዴሬሽን ም/ቤት መሆኑን የሚያነሱት የሕግ ባለሙያው፤ የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የሕግ ባለሙያዎች ስብስብ ሆኖ ም/ቤቱን የሚደግፍ እንደሆነ ገልጸዋል።

የፌዴሬሽን ም/ቤት ትርጉም እንዲሰጥ መነሻ የሆነውም "ሕገ-መንግሥቱን በትክክል ሊረዱ የሚችሉት ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ናቸው" በሚል እሳቤ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህ ሂደትም 'የፌዴሬሽን ም/ቤት ከፖለቲካ ነፃ ነው ወይ?' የሚሉና 'በፍርድ ቤት ያለፉ ጉዳዮች በም/ቤቱ ሲወሰኑ የፖለቲካ እሳቤ አይኖረውም ወይ?' የሚሉ ጥያቄዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።በጉዳዮ ብዙ ጊዜ ውይይት የሚደረግበትና ሀሳቦች የሚነሱበት እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ይህንንም በግልፅ ለመፍታት ወይም 'ምን መሆን አለበት?' የሚለው በሂደት እንደሚወሰን የገለጹት የሕግ ባለሙያው፤ እስካሁን ባለው የሕገ-መንግሥት ትርጉሙ ላይ በዋናነት የፌዴሬሽን ም/ቤት በሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ፣ ከጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንትና ም/ፕሬዝዳንት እንዲሁም ሌሎች ልምድ ባላቸው የሕግ ባለሙያዎች እንደሚደገፍ አንስተዋል።

ይህም የሕገ-መንግሥት እውቀት ያላቸው ባለሙያዎች ያሉበት እንደመሆኑ መጠን ሂደቱን እያገዘ መሆኑን ያነሱ ሲሆን፤ "ሕገ-መንግሥታዊ ፍ/ቤት ያስፈልጋል" ወደሚል ድምዳሜ ሲደረስ ግን ወደዚያው የመቀየር እድል መኖሩን ጠቁመዋል።

የፌዴሬሽን ም/ቤት በአመት ሁለት ጊዜ እንደሚሰበሰብ ያነሱት የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አባልና የሕግ ባለሙያ ደበበ ኃይለገብርኤል በበኩላቸው፤ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ልክ እንደ ፍርድ ቤት ሆኖ ውሳኔ ለመስጠት እንደማይችል ገልጸዋል።

ለዚህም ሲባል የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ተቋቁሞለ ምክረ ሀሳብ እንዲያቀርብለት መደረጉን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ቀደም ሲል በተለያየ ምክንያት የጉባኤው ሥራዎች ብዙ እንደማይታወቁ የሚገልጹት የሕግ ባለሙያው፤ በተጠናከረ መልኩ መንቀሳቀስ የጀመረው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ነው ብለዋል።

በዚህም መሠረት አሁን ላይ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮችን ጨምሮ በተለያዩ የሕግ ጉዳዮች ዙሪያ በርካታ ውሳኔዎች እንደሚወሰኑበት የገለጹ ሲሆን፤ በዓመት በአማካኝ ከ1 ሺሕ 500 እስከ 2 ሺሕ የሚደርሱ መዝገቦች ላይ ውሳኔ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ይህም በጉባኤውና በፌዴሬሽን ም/ቤት የሚሰጡ ውሳኔዎችን በፍርድ ቤት ተቀባይነት እንዲያገኙ የማድረግና በውሳኔው መሠረትም እንዲሰሩ የሚያስችል አወንታዊ ተፅዕኖዎችን እያመጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ