ሕዳር 25/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ለዓመታት በተደጋጋሚ ሲነሳ የቆየውና የግል ሠራተኞችን ክፍያ የሚወስነው በሀገር አቀፍ ደረጃ የዝቅተኛ ደመወዝ ወለል ቦርድ ሊቋቋም የመጨረሻ ሂደት ላይ መድረሱን፤ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን እና የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ለአሐዱ ሬድዮ አስታውቀዋል።

ለመንግሥት ሠተኛው ዝቅተኛ የመነሻ የደመወዝ ወለል መወሰኑንን የገለጹት የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ፤ ለግል ሠራተኞች ግን እስከአሁን አለመኖሩን አንስተዋል።

ኮንፌዴሬሽኑ ይህንን ጥያቄ ለረዥም ጊዜ ሲያቀርብ እንደቆየ ያስታወሱት ፕሬዝዳንቱ፤ አሁን ላይ በአሰሪ፣ ሠራተኛና በመንግሥት በጋራ የሚቋቋም ቦርድ መኖሩን ገልጸዋል።

ይህንን ቦርድ ለማቋቋም የሚወስነው ደንብ ላይም ውይይት ተደርጎበት ለጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት መቅረቡን ያስታወቁ ሲሆን፤ ደንቡ በሚኒስትሮች ም/ቤት ውሳኔ እንደሚፀድቅ ተናግረዋል።

ደንቡ እንደፀደቀም በሥስትዮሽ ማለትም ከአሰሪ፣ ሠራተኛና ከመንግሥት ጋር በመሆን ወደ ሥራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ሠራተኞች በተደጋጋሚ የዝቅተኛ ደመወዝ ወለል እንዲወሰን ለማድረግ ጥያቄ እንደሚያቀርቡ የገለጹት ደግሞ፤ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዳንኤል ተሬሳ ናቸው።

በመሆኑም መንግሥት ለጥያቄያቸው መልስ ለመስጠት ከሠራተኞችና አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን ጋር በመተባበር የዝቅተኛ ደመወዝ ወለልን የሚወስን ቦርድ እንዲቋቋም ለማድረግ ሕጎችን በማውጣት ወደ መጨረሻው ሂደት ላይ መድረሱን አስታውቀዋል።

የሚወጡ ሕጎች ተፈፃሚ ሆነው ካለቁ በኋላም በጥናት ላይ የተመሰረተ የዝቅተኛ ደመወዝ ወለል ቦርድ እንደሚቋቋም ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በማስረጃ ላይ የተመሰረቱ ሥራዎች እንደሚሰሩ ገልጸዋል። በዚህም የሠራተኞችን ችግር በመቅረፍ መብታቸውን ጠብቀው እንዲሰሩ ይደረጋል ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም ከዚህ በተጨማሪ ቀደም ሲል ለአሰሪዎችና ሠራተኞች ተግዳሮት የነበሩ ሕጎችን በማሻሻል ለሁሉም ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሰራበት እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በተለይም 'የግል ሠራተኞችን ጥያቄ ይመልሳል' ተብሎ የሚጠበቀው የዝቅተኛ ደመወዝ ወለል ውሳኔ ለማግኘት ወደመጨረሻው ሂደት ላይ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፤ በትክክል መቼ ውሳኔ ተሰጥቶበት እንደሚፀድቅና ወደሥራ እንደሚገባ ግን በግልጽ አልተነገረም።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ