ሕዳር 25/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) መካከል የዘላቂ ሰላም ስምምነት ተፈርሟል፡፡

በአፍሪካ ህብረት እና በኢጋድ አደራዳሪነት ወይይት እና ድርድር ሲካሄድ መቆየቱ የተገለጸ ሲሆን፤ በዚሁ መሰረት የክልሉ ርዕሰ መሰተዳድር አረጋ ከበደ እና የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅትን በመወከል ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ የዘላቂ ሰላም ስምምነቱን ተፈራርመዋል፡፡

Post image

ርዕሰ መሰተዳድሩ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ ዛሬ ለክልላችን ሕዝብ የመጀመሪያው ትልቅ የሰላም ኩነት የተካሄደበት ቀን ነው ብለዋል።

ከግጭት አሸናፊም ተሸናፊም የለም፣ ከሰላም ሁሉም ያተርፋል፣ ስምምነቱ ለሰላም ወዳድ ሕዝባችን ትልቅ እፎይታን ይሰጣል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የሕዝብና የመንግሥትን ጥሪ ተቀብለው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ለመጡ ወንድሞቻችን እንደ መንግሥት አድናቆትና ክብር አለኝ ብለዋል፡፡

Post image

የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅትን (አፋሕድ) በመወከል ስምምነቱን የተፈራረሙት ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ ባደረጉት ንግግር፥ ማንኛውም ግጭት መጨረሻው ውይይትና ድርድር ነው ብለዋል።

ችግሮችና የሀሳብ ልዩነትን በንግግር መፍታት ፖለቲካዊ ሽንፈት ሳይሆን ጥበብና ብልጠት መሆኑን ገልጸው፤ ችግሮችን ለመፍታት ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ማበር ተገቢ አለመሆኑን አስገንዝበዋል ሲል ኤፍ ኤም ሲ ዘግቧል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር አምባሳደር ሰልማ ማሊካ አዳዲ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ የሀገሪቱን ቀጣይ መዳረሻ የሚያቃና ነው ሲሉ ተናግረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ