ሕዳር 26/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ግጭት ባሉባቸው አካባቢዎች የሚፈጸሙ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን የሽግግር ፍትህ ፖሊሲውን መሠረት በማድረግ ምርመራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ፍትህ ሚኒስቴር ለአሐዱ ሬዲዮ አስታውቋል።
ጥቃቶች ሪፖርት እንዲደረጉ በልዩ ሁኔታ ምርመራዎችን የማድረግ ሥራ አለመቋረጡንና ለተጠቂዎች የሕክምና፣ የምግብና የመጠለያ ድጋፎች እየተደረገ እንደሚገኝ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሴቶች እና ሕጻናት ዴስክ ዳይሬክተር ዳግማዊት ተረፈ ተናግረዋል።
በሽግግር ፖሊሲው መሠረት የወንጀል ፍትሕ ስርዓቱን ከማየት በተጨማሪ አይነት ያላቸው ድጋፎች ለተጠቃሚዎች እንደሚደርጉ አብራርተዋል።
ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ የፍርድ ሂደት እራሱን ችሎ የሚታይ ቢሆንም፤ ዋናው ጉዳይ ጉዳት የደረሰባትን ሴት የሕክምናና የሥነ-ልቦና ድጋፍ ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።
በቅንጅት ምጣኔ ሀብታዊ ድጋፎች እንደሚደረጉም ጨምረው ገልጸዋል። በሽግግር ፍትህ ፖሊሲው መሠረት የሚፈጸሙ ወንጀሎች እየተጣሩ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
ግጭቶችን ባሉባቸው አካባቢዎች የሚፈጸሙ አስገድዶ መድፍር፣ ትንኮሳ እና ሌሎች ጾታዊ ጥቃቶች መባባሶችን የሚወጡ መረጃዎች ያስረዳሉ።
ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ የጾታዊ ጥቃት አይነቶች የሚባሉት የቤት ወስጥ ጥቃት፣ ኢኮኖሚያዊ ጥቃት፣ አካላዊ ጥቃት፣ ወሲባዊ ጥቃት እና ሥነ-ልቦናዊ ጥቃቶች የሚፈጸሙበት ሁኔታ እንዳለ ገልጸዋል።
ጾታዊ ጥቃትን በዘላቂነት ለመከላከል ሕጋዊ እርምጃ መጠናከር እና የሚወሰደው እርምጃ አስተማሪ መሆን እንዳለበት የጠቆሙት ኃላፊው፤ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትም ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ማህበረሰቡ ላይ የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣና የቅድመ መከላከል ሥራዎች እንዲሰሩ አሳስበዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን መሠረት በማድረግ ግጭት ባሉባቸው አካባቢዎች የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች ላይ ምርመራ እያካሄደ እንደሚገኝ ፍትሕ ሚኒስቴር ገለጸ