ጥቅምት 26/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው የኒውክሌር መሣሪያ ሙከራን እንደገና ትጀምራለች በማለት የሰጡት መግለጫን፤ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን "አሳሳቢ ጉዳይ" ነው ሲሉ ገልጸውታል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ዛሬ በክሬምሊን ከሩሲያ የጸጥታ ምክር ቤት ቋሚ አባላት ጋር ስብሰባ አድርገዋል።

በዚህ ስብሰባ ላይ 'አሜሪካ የኒውክሌር መሣሪያዎቿን መሞከር እንድትጀምር' ትራምፕ ለፔንታጎን መመሪያ መስጠታቸው "አሳሳቢ ጉዳይ ነው" ያሉት ፑቲን፤ "ሩሲያ ከኑክሌር ሙከራ እገዳ ስምምነት ለመውጣት ምንም አይነት እቅድ የላትም" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን የሁሉን አቀፍ የኒውክሌር ሙከራ እገዳ ስምምነት ተዋዋይ ወገኖች የኒውክሌር ሙከራዎችን ለማካሄድ ከወሰኑ፤ ሩሲያ ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ ትገደዳለች ሲሉ አሳስበዋል።
ፕሬዝዳንቱ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የልዩ አገልግሎት መሥሪያ ቤቶች እና አግባብነት ያላቸው ሲቪል ኤጀንሲዎች መረጃ እንዲሰበስቡ፣ በጸጥታው ምክር ቤት ቦታ ትንተና እንዲያካሂዱ እና የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ሙከራዎች ዝግጅት ላይ ሃሳብ እንዲያቀርቡም መመሪያ ሰጥተዋል።

የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስትር አንድሬ ቤሎሶቭ በበኩላቸው፤ "በኖቫያ ዜምሊያ የሙከራ ጣቢያ ለኑክሌር ሙከራዎች ወዲያውኑ ዝግጅት መጀመር ተገቢ ነው" ሲሉ አሳስበዋል፡፡
የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር በጥቅምት ወር ሩሲያ ላይ የሚሳኤል እና የኒውክሌር ጥቃት የመፈጸም ልምምድ ማድረጉንም ሚኒስቴሩ አስታውቀዋል፡፡
"አሜሪካ በአውሮፓ እና በእስያ-ፓስፊክ ክልል ውስጥ ሚሳኤሎችን ለማሰማራት አቅዳለች፣ ከጀርመን ወደ መካከለኛው ሩሲያ የሚወስደው የበረራ ጊዜ ከ6-7 ደቂቃዎች ነው" ሲሉም ቤሎሶቭ መናገራቸውን ስፑትኒክ ዘግቧል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ "ሌሎች ሀገራት የኒውክሌር ሙከራዎችን እያደረጉ ነው" በሚል ክስ፣ አሜሪካ ከሩሲያ እና ከቻይና ጋር "በእኩል ደረጃ" የኒውክሌር መሣሪያዎቿን መሞከር እንድትጀምር ለፔንታጎን (ለጦርነት ሚኒስቴር) መመሪያ መስጠታቸው ይታወሳል።
ይህ እርምጃ አሜሪካ እ.ኤ.አ ከ1992 ወዲህ ስትከተለው የነበረውን የኒውክሌር ሙከራ የማቆም የረጅም ጊዜ ፖሊሲ ሊሽር ይችላል ተብሏል።
ይህንንም ተከትሎ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለትራምፕ መግለጫ በሰጡት ምላሽ፤ "ሩሲያ ኒውክሌር ፍንዳታ ያዘለ ሙከራ አላደረገችም" ሲሉ ገልጸዋል።
እንደ ቡሬቬስትኒክ ያሉ የኒውክሌር አቅም ያላቸውን ሚሳኤሎች መሞከሯ፤ የኒውክሌር ሙከራ ተብሎ ሊወሰድ እንደማይገባም አብራርተዋል።
ፔስኮቭ ፕሬዝዳንት ፑቲን "ማንም ከከእገዳው ካፈነገጠ፣ ሩሲያም እንደዛው ትመልሳለች" ሲሉ ያስጠነቀቁትን አቋም ደግመው አሳስበዋል።
ትራምፕ በመመሪያቸው "የኒውክሌር ሙከራ" ሲሉ በትክክል "ሙሉ የኒውክሌር ፍንዳታ ነው ወይስ ሚሳኤሎችን መሞከር ብቻ" የሚለው ግልጽ ባይሆንም፤ የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር በኋላ ላይ አሜሪካ ለጊዜው የምትሰራው የኒውክሌር ፍንዳታ የሌለበትን ወይም ክፍሎችን የመፈተሽ ሥራ እንደሆነ ማብራሪያ ሰጥቷል።
ይህ የትራምፕ መግለጫ በኒውክሌር መሣሪያ ቁጥጥር ባለሙያዎች ዘንድ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል።
ይህ እርምጃ አዲስ የጦር መሣሪያ ግጭት ሊያስነሳ፣ ዓለም አቀፍ የኒውክሌር ሙከራ እገዳ ስምምነቶችን ሊያዳክም እና የዓለምን ሰላም አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችልም ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል።
በተጨማሪም የትራምፕ መግለጫ ከሰሞኑ በዩክሬን ጦርነትና በሌሎች ጉዳዮች ተባብሶ የመጣውን የአሜሪካና የሩሲያ ግንኙነት ይበልጥ እንዲወሳሰብ አድርጎታል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ