የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስን ጨምሮ የሃይማኖት ተቋማት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ አርሲ ዞን በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈፀመውን ግድያ በጽኑ አውግዘዋል።
በመግለጫቸውም መንግሥት የዜጎችን የመኖር ዋስትና የመጠበቅ ዋነኛ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ ጥቅምት 20 ቀን 2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ በምሥራቅ አርሲ ዞን በጉና፣ በመርቲ፣ በሸርካ እና በሆሎንቆ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች ላይ አሰቃቂ ግድያ መፈጸሙን ገልጿል።

በዚህም 25 የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በተኙበት ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን አመልክቷል።
ከትናንት በስቲያም በተመሳሳይ 5 የእምነቱ ተከታዮች ሲገደሉ፤ 3 ደግሞ መታገታቸውን ቤተክርስቲያኗ አስታውቃለች።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በዞኑ ሙስሊም ምዕመናን መገደላቸውን በመግለጽ፤ ግድያውን አውግዟል፡፡
የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንም ተመሳሳይ ድርጊት መፈፀሙን በመግለጽ፤ ግድያዎች እንዲቆሙና አጥፊዎች እንዲጠየቁ ጥሪ አቅርባለች።
በተጨማሪም በምዕራብ ወሎ መካነሰላም አካባቢ ከነበረ ውጊያ ማግስት፤ የእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ ግድያ መፈፀሙ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በበኩሉ፤ በአርሲ ዞን በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምዕመናን እና ካህናት፤ የሃይማኖት ተቋማት አገልጋዮች እና ምዕመናን ላይ ግድያና መፈጸሙን በመግለጫው አመልክቷል።

ይህንን ተከትሎም ጉዳዩን ከመሰረቱ የሚያጣራ ባለድርሻ አካላት ተወካዮች የተካተቱበት አጣሪ ቡድን አቋቁሞ ችግሩ ወደ የተከሰተባቸው ቦታዎች በመጓዝ ሥራውን መጀመሩን አስታውቋል።
የጉባኤው የሕዝብ ግንኙነት ጠቅላይ መመሪያ ኃላፊ መጋቢ ይታገሱ ኃይለሚካኤል ለአሐዱ በሰጡት ቃል፤ ልዑካኑ ከትላንት ጀምሮ ችግር ባለባቸው አራት ወረዳዎች ምልከታ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

መጋቢ ይታገሱ፣ ሕግ የማስከበር ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ቢሆንም ጉባኤው የተመለከታቸውን ልክ ያልሆኑ ጉዳዮች ሲመለከት ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሆነ ገልጸዋል።
ነገር ግን ሰላም የአንድ አካል ሥራ ባለመሆኑ ሁሉም ለሰላም ካልሠራ ለውጥ ይመጣል የሚል እምነት እንደሌላቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
ጉባኤው ለሕግ የበላይነት ማስከበር ኃላፊነት ላለበት መንግሥት ማሳወቅ ሥራውን እየሠራ መሆኑን ገልጸው፤ ሰላም ከመንግሥት ብቻ የሚጠበቅ አለመሆኑን ተናግረዋል።
በፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ባወጣው 09831መግለጫ፣ "በምሥራቅ አርሲ ዞን አስተዳደር የተፈፀመውን ጥቃት ኢ-ሰብዓዊ፣ እኩይና አፍራሽ ተግባር" ሲል አውግዞታል።

"የገዳዮቹና የአሰማሪዎቻቸው ዓላማ የሕዝቡን አንድነት በማናጋት ሀገርን ማፍረስ ነው" ሲልም ከሷል።
ይህ ዓይነቱ ድርጊት በተደጋጋሚ በተለያዩ ቦታዎች እየተከሰተ መምጣቱ የጉዳዩን አሳሳቢነት መግለጫ ያወጡ አካላት በሙሉ የገለጹት ነው።
የሕግ ባለሙያው አቶ አበባው ወርቁ በበኩላቸው፣ የመኖር መብት የማይገሰስ መብት መሆኑን ገልጸው፤ መንግሥትም የዜጎችን ሞትና ንብረት የማፍራት መብትን የማስከበር ሕገ-መንግሥታዊ ግዴታ ያለበት በመሆኑ ማስከበር ይገባዋል ብለዋል።
አቶ አበባው፣ "ሰዎች በማንነታቸውና በሚደግፉት አቋማቸው ምክንያት መገደል የለባቸውም" ሲሉ አሳስበዋል። በዋናነትም ሕጉ በግልፅ የተቀመጠ በመሆኑ ክፍተቱ የአፈጻጸም ችግር ከሆነ ማስፈጸሙ ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽህፈት ቤት የይግባኝ ሰሚ መንፈሳዊ ፍርድ ቤት መምሪያ ዳኛ ንቡረ-ዕድ አባ ዮሃንስ ገብረህይወት በበኩላቸው በፍቅር በመተሳሰብ መኖር እንደሚገባ ገልጸው፤ ራስ ወዳድነት መገዳደልንና ሕግ ጥሰትን የሚፈጥር በመሆኑ መንግሥት የሕግ መደላድል መፍጠር ይኖርበታል ሲሉ ተናግረዋል።

በአጠቃላይ፣ ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም የሚኖሩበት ሀገርን ለመፍጠር ሁሉም አካላት ሚና የሚጠይቅ መሆኑ ይታወቃል።
በዋናነት ደግሞ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ማስከበር እና የወንጀል ሕጎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቧል። ሆኖም ግን፣ ጥቃቶችን የፈፀሙ አካላት ወደ ፍርድ አለመቅረባቸው በሀገሪቱ ያለውን ሕግ የበላይነት አጠያያቂ እንዳደረገው ተገልጿል።
ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የፍትሕ ፕሮጀክት (WJP) ሪፖርት ላይ ከ38 የአፍሪካ ሀገራት ተካታ ከመጨረሻዎቹ 5 ሀገራት ተርታ እንድትመደብ ምክንያት ሆኗል።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ትላንትና በድጋሚ ባወጣው መግለጫ ላይ፤ አንዳንድ አካላት ኃላፊነት በጎደለው መልክና ባልተሟላ መረጃ በማኅበራዊ ሚዲያ መረጃ መስጠታቸውን አውግዞ፣ ይህ ተግባር የማጣራቱን ሂደት የሚጎዳ በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስቧል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ