ጥቅምት 25/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እስከ አውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 1 ድረስ ተግባራዊ የሚሆን፤ በሀገሪቱ የሚገኙትን ብርቅዬ የከበሩ ማዕድናትን የማውጣትና የማልማት ስልታዊ የድርጊት መርሃ ግብር እንዲዘጋጅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት (ካቢኔ) ትዕዛዝ መስጠታቸው ተነግሯል፡፡

የክሬምሊን ጽህፈት ቤት ዛሬ ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ፤ ሩሲያ የዓለም አቀፉን የብርቅዬ ማዕድናት አቅርቦት ገበያ መቆጣጠር በሚፈልጉ ሀገራት ላይ ያላትን ጥገኝነት ለመቀነስ የረዥም ጊዜ እቅድ በማውጣት ላይ ትገኛለች።

ብርቅዬ የከበሩ ማዕድናትን ከማውጣት እቅድ በተጨማሪን፤ ፑቲን የካቢኔው አባላት ከቻይና እና ከሰሜን ኮሪያ ጋር በሚያዋስኑ የድንበር አካባቢዎች ላይ የሚገኙ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ ግንኙነቶችን ለማልማት እና ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ እርምጃዎችን እንዲወስዱ አዘዋል።

በዚህም በድንበሮቹ አካባቢ "ባለብዙ-ዓይነት ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ማዕከላት" እንዲያቋቁም መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

በመመሪያውም ሩሲያን እና ቻይናን የሚያገናኙ ሁለት ነባር የባቡር ድልድዮች እንዲሁም፤ በ2026 ሥራ እንዲጀምር የታቀደ ወደ ሰሜን ኮሪያ የሚወስድ አዲስ ድልድይ መካተት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ትዕዛዙን አስፈላጊ ካደረጉ ዋና ዋና ምክንያቶችም፤ እነዚህ ብርቅዬ ማዕድናት ለዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች፣ ለስማርት ስልኮች፣ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እና ለጦር መሳሪያ ስርዓቶች ወሳኝ ግብዓት መሆናቸው ነው ተብሏል።

ሩሲያ በዓለም ላይ ትላልቅ የማዕድን ክምችት ካላቸው ሀገራት ውስጥ አምስተኛ ደረጃን ትይዛለች።

ይህ የፑቲን እርምጃ የመጣው ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት ምክንያት በተጣሉባት የምዕራባውያን ማዕቀቦች ሳቢያ ከምሥራቃዊ ጎረቤቶቿ ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ትስስር እያጠናከረች ባለችበት በዚህ ወቅት ነው።

እንደ እ.ኤ.አ በሚያዝያ ወር የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዩክሬን ጋር አንድ ስምምነት መፈራረማቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ይህም ስምምነት አሜሪካ በዩክሬን በሚገኙ አዳዲስ የማዕድናት ልማት ፕሮጀክቶች ላይ ቅድሚያ ተጠቃሚነት የምታገኝበትን መንገድ ይከፍታል።

ስምምነቱ "የአሜሪካ-ዩክሬን የመልሶ ግንባታ ኢንቨስትመንት ፈንድ" የሚል ስያሜ ተሰጥቶት፤ የዩክሬንን የተፈጥሮ ሀብት (እንደ ብርቅዬ ማዕድናት፣ ነዳጅና ጋዝ ያሉትን) በጋራ ለመጠቀምና የአሜሪካን የመልሶ ግንባታ ድጋፍ ለማረጋገጥ ያለመ ስለመሆኑ ተነግሯል።

ሩሲያ በበኩሏ በብርቅዬ ማዕድናት ፕሮጀክቶች ላይ ከአሜሪካ ጋር በአጋርነት ለመሥራት ፍላጎት እንዳላት ገልጻለች።

ይሁን እንጂ፣ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ለማስቆም በሚደረገው ጥረት በቂ መሻሻል አለመታየቱ ይህ ትብብር እውን እንዳይሆን አድርጎታል።

ሩሲያ 'ጦርነቱ ሳያበቃ ከአሜሪካ ጋር ትላልቅ የጋራ የማዕድን ፕሮጀክቶችን መጀመር አስቸጋሪ እንደሆነ' በመግለጿ፤ ጉዳዩ በእንጥልጥል ላይ እንዲቆይ ምክንያት ሆኗል።

በሌላ በኩል በከበሩ ማዕድናት ምርት ውስጥ ዋና ተዋናይ የሆነችው ቻይና፤ በዚህ ዓመት በአሜሪካ በተጣሉባት ታሪፎች ምክንያት በበቀል እርምጃ አጸፋዊ ምላሽ ሰጥታለች።

ይህ የበቀል እርምጃ ማዕድናቱን ወደ ውጭ የመላክ ሂደት ላይ ገደቦችን በመጣል ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን፤ ይህም የምዕራባውያን ቴክኖሎጂ አምራቾች ላይ ጫና የሚፈጥር መሆኑ ተነግሯል።

ሁለቱ የሩሲያ የሩቅ ምሥራቅ ጎረቤቶች ቻይናና ሰሜን ኮሪያ ምዕራባውያን በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ማዕቀብ ከጣሉበት ጊዜ ጀምሮ ከሞስኮ ጋር ያላቸውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር አጠናክረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ