ጥቅምት 25/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአሜሪካ 46ኛው ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩትና በዘመናዊ የአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸው ባለሥልጣን ከሚባሉት የፖለቲካ ሰዎች አንዱ የሆኑት ሪቻርድ ብሩስ ዲክ ቼኒ በ84 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

የቼኒ ቤተሰቦች ባወጡት መግለጫ ቼኒ ያረፉት ትናንት ምሽት (ሰኞ) መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ ለሞታቸው ምክንያት የሆነው የሳንባ ምች፣ የልብና የደም ቧንቧ በሽታዎች ሳቢያ የተፈጠሩ ውስብስብ ችግሮች መሆኑን አስታውቀዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።

ዲክ ቼኒ እ.ኤ.አ ከ2001 እስከ 2009 በፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ አስተዳደር ሥር፤ ለሁለት የስልጣን ዘመን ምክትል ፕሬዝዳንት በመሆን አገልግለዋል።

በተጨማሪም ከ9/11 ጥቃት በኋላ አሜሪካ "በሽብርተኝነት ላይ ያወጀችውን ጦርነት" በመቅረጽና በመምራት ረገድ ወሳኝ ሚና የተጫወቱ ሲሆን፤ በተለይም ኢራቅ "ጅምላ ጨራሽ መሳሪያ ታጥቃለች" በሚል ባካሄደችው ዘመቻ ላይ ዋና አማካሪ ነበሩ።

ቼኒ ምክትል ፕሬዝዳንትነት በተጨማሪ በፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ የስልጣን ዘመን፤ የመከላከያ ሚኒስትር፣ በፕሬዝዳንት ጄራልድ ፎርድ አስተዳደር ዘመን የዋይት ሀውስ ዋና የቢሮ ኃላፊ እና ለረጅም ጊዜ የዋዮሚንግ ግዛት ተወካይ ሆነው አገልግለዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ከራሳቸው ሪፐብሊካን ፓርቲ መሪ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በኃይል በመጋጨትና ትራምፕን በግልጽ በመተቸት በፓርቲው ውስጥ የውዝግብ ማዕከል ሆነው ቆይተዋል።

ቤተሰቦቻቸው በመግለጫቸው፤ ቼኒን "ታላቅና ጥሩ ሰው"፣ "ሀገራችንን እንድንወድ አስተምረውን የሄዱ ክቡር ታላቅ ሰው" በማለት ገልጸዋቸዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ