ጥቅምት 25/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በሦስት ወራት ውስጥ ብቻ በሕገ-ወጥ መንገድ ከተሰደዱ በኋላ የተለያየ ችግሮች ደርሶባቸው ከ530 በላይ ተጎጂ ስደተኞች፤ ወደ ሀገር መመለሳቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ አስታውቋል፡፡
በቢሮው የሥራ ስምሪት አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሰብሃዲን ሱልጣን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑና በሕገ-ወጥ መንገድ ወደተለያዩ ውጭ ሀገራት ከተሰደዱ በኋላ ለተለያዩ ችግሮች ተዳርገው የተመለሱ ተጎጂ ከስደት ተመላሾች ከ530 በላይ መሆናቸውን ገልጸው፤ ከእነዚህም መካከል ከ480 በላይ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን አብራርተዋል።
በዚህም ተጎጂዎች መልሰው እንዲቋቋሙ ለማድረግ መንግሥት በተያዘው በጀት ዓመት ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ መበጀቱን ተናግረዋል።
ከተመለሱት ተጎጂ ስደተኞች መካከል 160 የሚጠጉ ዜጎች ወደ ቋሚ ሥራ እንዲገቡ መደረጋቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
ቢሮው ማንኛውም ዜጋ በሕገ-ወጥ መንገድ እንዳይሰደድ ብሎም ሕገ-ወጥ ስደት ምን ያክል አስከፊ መሆኑን ለማህበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ከማስጨበጥ አንጻር በዚህ ሩብ ዓመት ከ130 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች መድረስ መቻላቸውን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
በሕገ ወጥ መንገድ የሚሰደዱ ዜጎች ለተለያዩ ችግሮች እየተጋለጡ በመሆኑ፤ ሁሉም ሰው ሕገ-ወጥ ደላሎችን እና መሰል የተሳሳቱ አመለካከቶችን መከላከል ይገባል ሲሉም የሥራ ስምሪት አገልግሎት ዳይሬክተሩ አጽንኦት ሰጥተውበታል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በመዲናዋ በሦስት ወራት ብቻ ከ530 በላይ የሚሆኑ ከስደት ተመላሽ ዜጎች ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሆነው ተመዝግበዋል ተባለ