ጥቅምት 28/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ፆታን መሠረት ላደረጉ ጥቃቶች ምላሽ የሚሰጡ ተቋማት በቁጥራቸውና በተደራሽነታቸው ውስን መሆን ችግሮችን ለመፍታት እንቅፋት ሆኗል ሲል የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
በሚኒስቴር መ/ቤቱ ዓለም አቀፍ የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ቀንን ምክንያት በማድረግ የጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል እና በሁሉም ማህበረሰብ ዘንድ ግንዛቤ እንዲኖር ለማድረግ ከመገናኛ ብዙሐን አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
በዚህም በሚኒስቴር መ/ቤቱ የሴቶች መብት ጥበቃና ምላሽ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘካሪያስ ደሳለኝ፤ ፆታን መሠረት ላደረጉ ጥቃቶች ምላሽ የሚሰጡ ተቋማት በቁጥራቸውና በተደራሽነታቸው ውስን መሆን ችግሮችን ለመፍታት እንቅፋት ሆኗል ብለዋል፡፡

ሚኒስቴር መ/ቤቱ ዓለም አቀፍ የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ቀንን ምክንያት በማድረግ በየዓመቱ በሚያካሂደው የግንዛቤ እና ንቅናቄ ሥራ ተጎጂዎች የተቀናጀ ድጋፍ እንዲያገኙና ወደ ቀደመ ሕይወታቸው እንዲመለሱ የሚያግዙ ተግባራት ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሚከበርም አያይዘው ገልጸዋል፡፡
ለ20ኛ ጊዜ የሚከብረው ይኸው ዓለም አቀፍ የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ቀን "ጥቃትን የማይታገስ ማህበረሰብ ለትውልድ ግንባታ" በሚል መሪ ቃል ከሕዳር 16 እስከ ታህሳስ 1 ቀን2018 ዓ.ም ይከበራል ብለዋል፡፡
ዕለቱ በየደረጃው በሚገኙ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ሕብረተሰቡ ጥቃትን ያለመታገስ አቋም በሚያሳይ መልኩ በተለያዩ መርሀ-ግብሮች እንደሚከበር ተናግረዋል፡፡
በዚህም መሠረት ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል ለ55 ሚሊዮን ሰዎች ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ለመስራት መታቀዱን መሪ ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል።
በተጨማሪም ዓለም አቀፉ የሕጻናት ቀን ሕዳር 11 የሚከበር መሆኑንም በማስመለከት፤ የሕጻናት እና ሴቶች ጥቃትን በጋራ መከላከል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
በተለይ በሁሉም ዩንቨርስቲዎችና ትምህርት ቤቶች፣ ምክር ቤቶች በሐይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የጎሳ መሪዎች፣ አባ ገዳዎች፣ በሁሉም በሥራ ቦታዎች ሁሉም የፍትህ አካላት ምክክር ለማካሄድ በታቀዱን አብራርተዋል።
በተጨማሪም የተለያዩ የሴት አደረጃጀቶች ጥቃትን እንዲከላከሉና እንዲያወግዙ ሰፊ የንቅናቄ ዘመቻ ማድረግ፣ ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጠናከር፣ ሀብት ማሰባሰብና ድጋፍ ማድረግ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ በወጣው መሪ-ቃል መሰረት የመገኛኛ ብዙሃን ዘመቻ የሚካሄድ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ