ጥቅምት 28/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ የትግራይ የጸጥታ ኃይሎች ወደ አፋር ክልል ዘልለው በመግባት በንጹሃንን ዜጎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን በመግለጽ ያወጣውን መግለጫ፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር "መሠረተ ቢስ እና ያልተረገጠ ነው" ሲል አስተባብሏል።
የአፋር ክልል መንግሥት ረብዕ ጥቅምት 26 ቀን 2018 ማምሻውን ባወጣው መግለጫ "የህወሓት ቡድን ኃይሎች የአፋር ክልል ወሰንን ዘልቀው በመግባት 6 መንደሮችን በጉልበት መቆጣጠራቸውን" በመግለጽ፤ ንፁሃንን ዜጎችን በሞርታር መደብደባቸውን በዚህም የፕሪቶሪያውን ስምምነት ማፈረሳቸውን ማስታወቁ ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጉዳዩን አስመልክቶ፤ ትናንት ሐሙስ ጥቅምት 27 ምሽት ላይ መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫውም፤ "ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ ሰላማዊ እና ፖለቲካዊ ሂደቶችን የሚያውኩ እና የፕሪቶሪያን ስምምነትን የሚጎዱ እድገቶችን እያየን ነው" ብሏል።
"ሆን ተብሎ መድረክ በመፍጠር፣ በመደገፍና ተልዕኮ በመስጠት በአፋር ክልል የታጠቁ ቡድኖችን በማስታጠቅ ትግራይን ለጥፋትና እርስ በርስ ለማባላት በትግራይ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ተደርገዋል" ሲልም ከሷል።
"በአፋር ክልል "በነጻ መሬት" የታጠቁ ሃይሎች ባለፈው ዓመት እና በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ላይ በኮኔባ እና አባአላ አቅጣጫ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን እየፈፀሙ ነው" ያለው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤ የመቀሌ-መኮኒ መስመርን ለማዘግየት ጊዜያዊ የአስተዳደር አመራር አካላት እርምጃ ሲወስዱ መቆየታቸውን ገልጿል።
"የክልሉ ሕዝብና ጊዜያዊ አስተዳደር ግን የውስጥ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ እና በውይይት ለመፍታት ካላቸው ከፍተኛ ፍላጎት የተነሳ፤ ሁኔታውን ከመግለጽ ተቆጥበዋል" ያለም ሲሆን፤ "አሁንም በትግራይ በኩል ሁከትና አለመረጋጋት አንፈልግም" ሲል አስታውቋል
ስለሆነም የአፋር ክልል መንግሥት ያወጣው መግለጫ፤ "መሠረተ ቢስ እና ያልተረገጠ የአፋር ድንበር ለሁለቱ ሕዝቦች ሰላማዊና ታሪካዊ ወንድማማችነት እና ሰፈር ተስማሚ አይደለም ሲል አጣጥሎታል።
አክሎም፤ "አንዱን ወይም ሌላውን እየደገፉና እያስተናገዱ ትግራይን የጦር አውድማ ለማድረግ የሚጥሩ፤ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በውስጣችን ጥርጣሬ እንዲፈጠር የተለያዩ ሰበቦችን የሚጠቀሙ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስቧል።
"የትግራይን ችግር በዘላቂነት በትግራይ እና በትግራይ ተወላጆች መፍታት ይቻላል" ብሎ በፅኑ እንደሚያምን የገለጸው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤ "በውስጣዊ የፖለቲካ ችግሮች ምክንያት የሃሳብ ልዩነት የተለመደ መሆኑን በማሰብ ችግራችንን በውይይት እና በስምምነት ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋግጣል" ብሏል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዘላቂ ደህንነትና ዘላቂ ሰላም ሊገኝ የሚችለው የፕሪቶሪያ ስምምነትን በጥብቅ በመተግበር ብቻ እንደሆነ በፅኑ ያምናል ሲልም አስታውቋል።
ስለሆነም፤ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እና የፕሪቶሪያ ስምምነትን ያለምንም መዘግየት ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ የፕሪቶሪያ ስምምነትን በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲደረግ፣ የትግራይን ሕገ-መንግሥታዊ ድንበሮች እንዲረጋገጥና እና ሕዝቦች በሰላም ወደ ቀያቸው እንዲመለሱም በመግለጫው ጥሪ አቅርቧል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ