የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ የፈፀማቸው ድርጊቶች ወደ ጦርነት ለመግባት ከበቂ በላይ ምክንያቶች እንደሆኑ መግለጻቸው ይታወሳል።
ኤታማዦር ሹሙ ከ5 ዓመት በፊት በትግራይ ውስጥ በነበረው የሀገሪቱ ጦር ሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ለመዘከር ጥቅምት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. በተካሄደው መድረክ ላይ ባደረጉት ንግግር በህወሓት ላይ ክሶችን ሰንዝረዋል።

"ህወሓት ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ የሰራቸው ትንኮሳዎች እና ሴራዎች ወደ ጦርነት ለመግባት በቂ ናቸው ከበቂም በላይ ናቸው" ሲሉ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ መልኩ፤ ህወሓት "የኢትዮጵያ መንግሥት ሌላ ዙር ጦርነት ለማካሄድ ግልጽ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው" ሲል መክሰሱ የሚታወስ ነው። ህወሓት ባወጣው መግለጫውም "የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህንን እንቅስቃሴ እንዲያስቆም" ሲል ጠይቋል።
በኢትዮጵያ የሚገኘው የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ከ22 የአውሮፓ ህብረት ሀገራት እና ኖርዌይ ጋር በመሆን፤ ከመጪው አጠቃላይ ምርጫ በፊት በፕሪቶሪያ ስምምነት ፈራሚዎች መካከል ፖለቲካዊ ንግግር እንዲቀጥል በጋራ ባወጡት መግለጫ ጠይቀዋል።
ይህ እንዲህ ባለበት ሁኔታ፤ በአፋር ብሔራዊ ክልል "ህወሓት ድንበር ጥሶ ጥቃት ፈጽሞብኛል" ሲል ትላንት ምሽት ባወጣው መግለጫ ከሷል።

ክልሉ "ህወሓት ወሰን ውስጥ በመግባት 6 መንደሮችን በጉልበት በመቆጣጠር ንጹሐንን በሞርታርና በዙ-23 በመደብደብ የተለመደውን የሽብር ተግባሩን በግልጽ ጀምሯል" ሲል ክስ አቅርቧል።
ይህንን የክልሉን ክስ በተመለከተ ከፌደራል መንግሥት የተሰጠ ምንም ዓይነት መግለጫ የሌለ ሲሆን፤ በህወሓት በኩልም የተሰጠ ማስተባበያ የለም።
ነገር ግን በቅርቡ የመመሰረቻ ጉባኤውን በአዲስ አበባ ያደረገው የዲሞክራሲ ስምረት ትግራይ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፤ ጥቃቱን በመኮነን መግለጫ አውጥተዋል።

ይህ አካሄድ ጉዳዩን አሳሳቢነት የሚያሳይ ሲሆን፤ ወደ ዳግም ሌላ ዙር ጦርነት ላለመግባት በሚደረገው ጥረት ላይ ውሃ የሚከልስ እንዳይሆን ተሰግቷል።
አቶ ወልዱ ተሾመ በትግራይ ክልል የከውጥ ፈላጊ ወጣቶች አባል ሲሆኑ፤ በመቀሌ እና ዙሪያው ውጥረት መከሰቱን ገልጸዋል።
ጥቅምት ወር በአጠቃላይ ስጋት የደቀነበት እንደነበር በማንሳት፤ ዜጎች በባንክ ቤት እና የገበያ ሽመታ ላይ ተጠምደው ይገኛሉ ሲሉ ሁኔታውን ይገልጻሉ።
የአፋር ክልል ህወሓት በዞን ሁለት በመጋሌ ወረዳ ቶንሳ ቀበሌ ዋራዓ እና ሚልኪ በሚባሉ ልዩ አካባቢዎች ወሰን ተሻግሮ በመግባት ከምሽቱ አንድ ሰዓት አካባቢ በንጹሐን የአፋር አርብቶ-አደሮች ላይ የከባድ መሳሪያ ተኩስ በመክፈት የፕሪቶሪያ ስምምነትን በግልጽ አፍርሷል ሲል ገልጿል።
አቶ ወልዱ ተሾመ በትግራይ እየተስተዋለ ያለው ሁኔታ በጣም ስጋት የሚፈጥር መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ "ወጣቱ ጦርነት ሰልችቶታል" ብለዋል።
አሁን እየሆነ ያለው ሁኔታም በአፋር በኩል የተደረገው እንቅስቃሴ ወጣቱ ከክልሉ የሚወጣበትን መንገድ የመዝጋት አካሄድ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በአሁን ወቅት በአማራ ክልል የሚደረገውን ውጊያ ጨምሮ በኦሮሚያ ክልል ያለው ግጭት መፍትሄ እንዲበጅለት ሲጠየቅ ቆይቷል።

ይሁን እንጂ ይህ ችግር ሳይፈታ አሁን በትግራይ ክልል ኃይሎችና በ"ነፃ መሬት" በሚል ጫካ ካሉ አካላት ጋር የተፈጠረው ግጭት ሌላ መልክ እየያዘ መምጣቱ ያሳያል።
ይህ እንቅስቃሴ ደግሞ በዋናነት በአፋር ክልል ውስጥ እየተደረገ መሆኑን ትግራይንና አፋርን ክልል የግጭት ቀጠና እንዳያደርግ ስጋትን ፈጥሯል።
የዳጉ ኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጥምረት ፕሬዝዳንት አቶ አደም ቦሪ፤ "ኢትዮጵያ ሁሉን አካታች ውይይት ያስፈልጋታል" ብለዋል።
"የሃሳብ ልዩነት ያለ የሚኖር ነው" ያሉም ሲሆን፤ በአፋር ክልልም ግጭቶች የሚበራከቱ ከሆነ ሀገሪቱ ያሰበችውን ምክክር ላታሳካ ትችላለች ሲሉ ሃሳባቸውን ይናገራሉ።
በአፋር ክልል የሚገኙት ታጣቂዎች እራሳቸውን "ትግራይ ሰላም ሠራዊት" ሲሉ የጠሩ ሲሆን፤ ህወሓትን በመቃወም በትጥቅ ትግል ለውጥ ለማምጣት ያስባሉ።
ነገር ግን ከመጀመሪያው "ነፃ መሬት" ብለው የተቀመጡበት ቦታ አፋር ክልል መሆኑ እየታወቀ ነፃ መሬት ብለው መደራጀታቸውን የሚኮንኑም አሉ።
ሌላው የአፋር ነፃ አውጪ ግንባርም በቅርቡ ወደ ኤርትራ የሸሸ ሲሆን፤ በኤርትራ ውስጥ እራሱን እያደራጀ መሆኑ ይገለጻል። ይህ ደግሞ በክልሉ የሚከሰቱ አለመግባባቶችን በከፍተኛ ስጋት እንዲታዩ የሚያደርጋቸው መሆናቸውን አቶ አደም ቦሪ ጨምረው ይናገራሉ።
የአፋር ብሔራዊ ክልል በትላንቱ መግለጫው፤ "ከጥፋቱ የማይማረው ህወሓት" ሲል የገለጸው ቡድን ከድርጊቱ በአስቸኳይ ሊቆጠብ እንደሚገባ አሳስቧል።
የዜጎች ደህንነትና የወሰኑን ክብር የማስጠበቅ እንዲሁም ራስን ከማንኛውም ውጫዊ ጥቃት የመከላከል ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አስጠንቅቋል።
የሰሞኑ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ሦስተኛ ዓመት አስመልከቶ መግለጫ ሰጥቶ የነበረው ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ኢትዮጵያ፤ "ሁሉም አካላት የጦርነትን አስከፊነት አስመልከቶ ዘመቻ መጀመር አለባቸው" ሲል ገልጿል።
የድርጅቱ ፕሬዝዳንት አቶ ተስፋዓለም በርህ እንደገለጹት፤ ማንኛውም ሰው አውቆም ይሁን ሳያውቅ ለጦርነት ከሚያደርገው ድጋፍ እራሱን ሊያቅብ ይገባል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላም የሰሜኑን ጦርነት አምስተኛ ዓመት አስመልከቶ ባደረጉት ንግግር፤ ለህወሓት ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። "ለጦርነት አንቸኩልም ነገር ግን በሰላማችን እና በብሔራዊ አንድነታችን የመጣን እንዋጋለን" ሲሉም ጠንከር ያለ መልዕክት አስተላልፈው ነበር።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ "ህወሓት ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ የፈጸማቸው ድርጊቶች ዳግም ጦርነት ለመጀመር ከበቂ በላይ ምክንያት ናቸው" ሲሉ ክስ ሰንዝረዋል። ህወሓት በበኩሉ "መንግሥት ለሌላ ዙር ውጊያ እየተዘጋጀ ነው" ሲል በመክሰስ ምላሽ ሰጥቷል።
ይህ ከፍተኛ ውጥረት ባለበት ሁኔታ፤ የአፋር ክልል ህወሓት ድንበር ጥሶ ንጹሐንን በከባድ መሳሪያ መደብደቡንና መንደሮችን መቆጣጠሩን በይፋ ከሷል።
ይህ ክስ "የሰላም ስምምነቱን አፍርሷል" የሚል ስጋት ፈጥሯል፤ የዲሞክራሲ ስምረት ትግራይ ፓርቲም ጥቃቱን ኮንኗል። በትግራይ ክልል የአካባቢው ነዋሪዎችና ወጣቶች ጦርነት እንደሰለቻቸውና ውጥረት እንዳለ መስክረዋል።
የአውሮፓ ሕብረትና ሲቪል ማኅበራት በአፋር ያለው ግጭት የሀገሪቱን ሁሉን አካታች ውይይት እንዳያደናቅፍ ፖለቲካዊ ንግግር እንዲቀጥል አጥብቀው ይጠይቃሉ።
ሌሎች ታጣቂ ቡድኖችም በክልሉ መኖራቸው ስጋቱን አባብሶታል። የሰላም ስምምነቱ ሦስተኛ ዓመት እየታሰበ ባለበት ወቅት በአፋር ክልል የተከሰተው ይህ ግጭት፤ በጦርነት ያላገገሙትን ክልሎች ዳግም ወደ ውጊያ እንዳይመልስ የሁሉንም ትኩረት ሳቧል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ