ሕዳር 1/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም አቅጣጫዎች የሚደረገው በጦር መሳሪያ የታገዘ ግጭት በአስቸኳይ እንዲቆም 'ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ኢትዮጵያ' የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ የተራድኦ ድርጅት ጥሪ አቅርቧል።
ድርጅቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሰላም ወዳድ "ጦርነት አያስፈልግም" የሚል ዘመቻ በያለበት እንዲጀምር አሳስቧል።
"ከሕዝቡ የሞራል፣ የገንዘብና የጉልበት ድጋፍ ካላገኙ ተዋጊ ኃይሎች ብቻቸውን ጦርነት ሊያካሂዱ አይችሉም" ያለው ማኅበሩ፤ መገናኝ ብዙኃን፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ጨምሮ በውስጥም በውጭም ያለው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ "ጦርነት ይበቃል" እንዲል ሐሳብ አቅርቧል።

የቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዓለም በርኸ፤ "በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮምያ ክልሎች ያለውን ጨምሮ በመላው ኢትዮጵያ በጦር መሳሪያ የታገዘ ደም አፋሳሽ ግጭት እንዲቆም ሕዝብ መተባበር አለበት" ብለዋል።
ሕዝቡ ጦርነት የማስቆም ጉልበቱን እንዲጠቀም ያሳሰቡት አቶ ተስፋዓለም፤ "የእርስ በእርስ ጦርነት የሚያመጣውን ጉዳት በሚገባ የቀመስን ህዝቦች ነን" ብለዋል።
በተለይ በሕወሓት እና በፌዴራል መንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ መካረሩ ከፍተኛ ስጋት እንደፈጠረባቸው የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ 'ሀገሪቱ ዳግም ወደ ጦርነት ትገባለች' የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል።
በመሆኑም፤ ሁሉም ወገኖች ጦርነት የሚያስከትለውን ጉዳት በመገንዘብ ከጠብ አጫሪ እና ጦርነት ቀስቃሽ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ