ሕዳር 1/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ኦቪድ ሪል እስቴት ከሕዳር 22 እስከ ታሕሳስ 6 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ አምስት የተለያዩ ቦታዎች ለ15 ቀናቶች የሚቆይ ታላቅ የሽያጭ ኤክስፖ ማዘጋጀቱን አስታውቋል።

ይህ የሽያጭ ኤክስፖ ሊዘጋጅበት የቻለው ዋና ምክንያት ከዚህ ቀደም ከኦቪድ ቤት እና የንግድ ቦታዎችን ለሚገዙ ሰዎች ተደርጎ የነበረው የዋጋ ቅናሽ ከታሕሳስ 7 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የዋጋ ማስተካከያ ስለሚደረግበት መሆኑን የኦቪድ ሪል እስቴት ማርኬቲንግ ማኔጀር ወ/ሮ መቅደስ ቀደመ ገልጸዋል።

Post image

በዚህም መሠረት በገርጂ ፊደራል ቤቶች ኦቪድ ግቢ ውስጥ፣ በገላን ጉራ ሳይት፣ በአራት ኪሎ ጥይት ቤት ሳይት፣ ኢትዮ ኩባ አዳራሽ እና ጎልፍ ክለብ ኤክስፖው የሚካሄድ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የተለያዩ የመኖሪያ ቤቶችና የንግድ ሱቆች በቅናሽ ዋጋ ለሽያጭ የሚቀርቡ ሲሆን፤ አመቺ የክፍያ ስርዓቶችም በአማራጭነት መቅረባቸውን አክለዋል።

በመሆኑም ከታሕሳስ 7 ጀምሮ የዋጋ ጭማሪ ስለሚኖር በዚህ ኤክስፖ ቤት ለመግዛት የሚፈልግ ሁሉም ሰው የዋጋ ቅናሹን ዕድል ለመጨረሻ ጊዜ መጠቀም እንደሚችል ጠቁመዋል።

የተደረገው ቅናሽ በመጠን ምን ያክል እንደሆነ ለጊዜው አለመወሰኑን ያነሱት ማርኬቲንግ ማናጀሯ፤ ነገር ግን ከዚህ ቀደም ሲደረጉ ከቆዩት የቅናሽ ኤክስፖዎች በሙሉ የበለጠ ቅናሽ የሚካሄድበት እንደሆነ ገልጸዋል።

"ራዕያችን ልማት ነው" የሚል መርህ አንግቦ የተነሳው ኦቪድ ሪል እስቴት፤ ደረጃቸውን የጠበቁ የመኖሪያ ቤቶችን በጥራትና በፍጥነት እየገነባ ለእያንዳንዱ ዜጋ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ በኮንስትራክሽንና ሪል እስቴት ዘርፉ ላይ ሽግግር የመፍጠር ተልዕኮውን ለማሳካት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

እንዲሁም ሪል እስቴቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚታየውን የመኖሪያ ቤቶች አቅርቦት ችግር ለማቃለል ባለፉት ዓመታት ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ወ/ሮ መቅደስ አንስተዋል።

"በዚህም ብዙዎችን ተጠቃሚ ያደረጉና በዘርፍ ደረጃ ትልቅ ተጽዕኖ መፍጠር የቻሉ ተጨባጭ ውጤቶችን ለማስመዝገብ ችሏል" ብለዋል።

ኦቪድ ሪል እስቴት 'አልሙኒየም ፎርምወርክ' የተባለውን ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂ ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት በገርጂ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ቤቶች ፕሮጀክት 500 ቤቶችን፣ በተቋማዊ የማህበራዊ ኃላፊነት ፕሮጀክቶች ደግሞ 205 ቤቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቅቆ ማስረከቡን ገልጸዋል።

በዚህም ባለፉት ዓመታት በራሱም ሆነ በመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነት ሞዳሊቲ ተግባራዊ ባደረጋቸው ፕሮጀክቶች በሺህዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን ገንብቶ ማጠናቀቅ መቻሉን አንስተዋል፡፡

ከእነዚህም መካከል በአቧሬ መልሶ ማልማት ፕሮጀክት በ100 ቀናት ገንብቶ ያጠናቀቃቸውና ለባለቤቶች ያስረከባቸው የመኖሪያና የንግድ አገልግሎት የሚሰጡ ባለ ጂ ፕላስ 12 ወለል 7 ዘመናዊ ሕንጻዎችን ጠቅሰዋል።

"በተጨማሪም ከሳምንታት በፊት በጥይት ቤት ፕሮጀክት ለቤት ገዢዎች ያስረከባቸው 167 ቤቶች የኩባንያው ስኬታማ ጉዞ ቀጣይነት ማሳያዎች ናቸው" ሱሉ ገልጸዋል።

ኦቪድ ሆልዲንግ ቤቶችን በጥራትና በፍጥነት እየገነባ ለዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ በመቻሉም በየዓመቱ ከ25 እስከ 30 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ይታይበት የነበረውን የሀገሪቱ የቤቶች ገበያ ዋጋ ከማረጋጋት ባለፈ፤ ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ እንዲፈጠር በማድረግ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ማሳደር ችለዋል ብለዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ኦቪድ ግዙፉን የገላን ጉራ ከተማ ፕሮጀክት ጨምሮ በአዲስ አበባና በሌሎች የአገራችን ከተሞች በርካታ ሰፋፊ ፕሮጀክቶችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ማርኬቲንግ ማኔጀሯ፤ በገላን ጉራ ፕሮጀክት በ570 ሄክታር መሬት ላይ 60 ሺህ ቤቶችን በመገንባት ከተማን እየመሰረተ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

"ኦቪድ ሆልዲንግ በሥሩ በሚገኙት ኩባንያዎች በድምሩ ከ10 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ግዙፍ ኩባንያ ሲሆን፤ በታማኝ ግብር ከፋይነት ለአገራዊ ልማት የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ በተደጋጋሚ ለሽልማት የበቃ ተቋም ነው" ሲሉም ገልጸዋል።

ከዚህ ባሻገርም በተለያዩ የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎች በርካታ ቤቶችን በመገንባት የበጎ አድሬጎት ሥራዎች ላይ በስፋት እየተሳተፈ እንደሚገኝ ተነግሯል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ