ሕዳር 22/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የጥናትና ምርምር ሥራዎች የተማረው ማኅበረሰብ ወይም የተመራማሪዎች ተግባር ብቻ ተደርጎ መታሰቡ፤ የተሳሳተ አረዳድ እንደሆነ የማኅበራዊ ዘርፍ ተመራማሪዎች ገልጸዋል።

አመለካከቱ በመረጃ አሰባሰብ ወቅት ትክክለኛ መረጃ እንዳይገኝ እንቅፋት ፈጥሯል ተብሏል፡፡

"ሊያጠናው የፈለገውን ዘርፍ በቅጡ የተረዳ እና ማሳየት የፈለገውን ክፍተት የተገነዘበ ማንኛውም ሰው የምርምር ቅደም ተከተሉን አክብሮ በማንኛውም ዘርፍ ጥናት ማካሄድ ይችላል" ያሉት ባለሙያዎቹ፤ "ሰዎች ለጥናት መጠይቆች ሐሳብ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸው እንዲሁም ምርምርን የተወሰኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ኃላፊነት ብቻ ተደርጎ መታሰቡ ሀገር በቀል መፍትሔዎች እንዲቀንሱ አድርጓል" የሚል ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡

Post image

በማኅበራዊ ዘርፍ የጤና ነክ ጉዳዮች ተመራማሪ አዳሙ አዲሴ (ዶ/ር) በጥናት እና ምርምር ሥራዎች ውስጥ ከሚያጋጥሙ እንቅፋቶች መካከል ዋንኛው፤ ለችግሮች መፍትሔ የሚያፈላልጉ ጥናቶችን ማካሔድ የአንድ ሰው ወይም የተወሰነ ቡድን ወይም የከፍተኛ ምሁራን ሥራ ብቻ እንደሆነ መታሰቡ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ዶ/ር አዳሙ አክለውም፤ "ለምርምር ሥራዎች የሚመደበው በጀት፣ የሚመረጠው ርዕሰ ጉዳይ እና ሌሎች አስፈላጊ ግብአቶች በውጭ ሀገራት ወይም ተቋማት መታገዙ የሀገርን ተጨባጭ ችግር መፍታት እንዳይቻል አድርጓል" ብለዋል፡፡

ሌላኛው የጤና ነክ ጉዳዮች ዘርፍ ተመራማሪ መለሰ ጌጡ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ "ለጥናት እና ምርምር ሥራዎች እንቅፋት ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የበጀት እጥረት፣ ያልተነካ ርዕሰ ጉዳይ ማጣትና የገንዘብ ድጋፍ በሚያደርጉ ተቋማት ፍላጎት ላይ መመስረት ይገኙበታል" ብለዋል፡፡

"የምርምር ሥራዎች ችግር በተመራማሪዎችና በውሳኔ ሰጪዎች መካከል ያለው ክፍተት ነው" ያሉት ደግሞ፤ በጤና ሚኒስቴር የፖሊሲ ስትራቴጂ ጥናትና ምርምር መሪ ሥራ አስፈጻሚ መሐመድ አሊ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

"ተመራማሪዎች የምርምር ሥራዎቻቸውን ውጤት መከታተል የሚያስችላቸው አሰራር የለም" የሚሉት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ "ውሳኔ ሰጪ የመንግሥት አካላት በተለይ የሀገር ውስጥ ጥናት እና ምርምርን ተቀብለው ተግባራዊ የማድረግ ፈቃደኝነት የላቸውም" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች ቅድሚያ ከሚሰጧቸው አራት የምርምር መርሆዎች መካከል ዓለም አቀፍ ደረጃን መጠበቅ፣ ለማኅበረሰብ ጠቀሜታ ያለው መሆን፣ ለላቀ ምርምር ክፍት መሆንና ለተመራማሪዎች የተመቻቸ የምርምር አካባቢ መፍጠርን ትኩረት በማድረግ እየሠሩ ይገኛሉ ተብሏል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ