ሕዳር 22/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የአብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ሕገ-መንግሥት የቅኝ ገዢዎቻቸውን ሐሳብና ፍላጎት የሚያንጸባርቅ መሆኑ እና በአግባቡ አለመተግበሩ አህጉሪቱን ለከፋ ጦርነት፣ ግጭትና ተደጋጋሚ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ዳርጓታል ሲሉ የሕግ ባለሙያዎች ተናግረዋል።

ባለሙያዎቹ እንደሚሉት፤ የአፍሪካ ሀገራት የሚመሩበት ሕገ-መንግሥታቸው አወቃቀር ከአፍሪካውያን ተጨባጭ እውነታ ጋር ላለመጣጣሙ ዋነኛ ምክንያት፤ የሕገ-መንግሥቱ አንቀጾች ከሀገሪቱ ሕዝቦች በላይ የቅኝ ገዢ ሀገራትን ፍላጎት ለማስጠበቅ በሚመች መልኩ ስለተቀረጹ፣ የአፍሪካውያንን አስተሳሰብ ስለማያንጸባርቁ እንዲሁም ያሉትም ሕገ-መንግሥቶች ቢሆኑ በትክክል ስለማይተገበሩ ነው።

ይህ አቋም የተገለጸው በ4ኛው የአፍሪካ ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶች እና መሰል ተቋማት ዓለምአቀፋዊ ሲምፖዚየም ላይ ተሳታፊ በነበሩ የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አባላት ነው።

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አባልና የሕግ ባለሙያ አቶ ምትኩ ማዳ፤ "አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ነጻነታቸውን ሲያገኙ ሕገ-መንግሥት በሚያዘጋጁበት ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ከቅኝ ግዛት ተጽዕኖ ነጻ መሆን አልቻሉም" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል።

አክለውም፤ "በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሕገ-መንግሥታቸውና በመንግሥት አወቃቀራቸው ጭምር የቀድሞ ቅኝ ገዢዎቻቸው ተጽዕኖ ይስተዋላል። በተለይም የመንግሥት ሥልጣን እና ተግባራትን በሚመለከት የተቀመጡት ደንቦች ከቅኝ ግዛት ተጽዕኖ አለባቸው" ብለዋል።

በአፍሪካዊ ሀገራት ሕገ-መንግሥቶች ላይ የተቀመጡት ድንጋጌዎች ከአፍሪካውያን ባህልና ልምድ እንዲሁም፤ ከየሀገራቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የማይስማሙ፣ ነገር ግን ከቅኝ ገዢዎች ፍላጎት ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን ያነሱት አቶ ምትኩ፤ "በአፍሪካ ለሚከሰቱ ችግሮች ሁሉ ሕገ-መንግሥት ተጠያቂ ባይሆንም፤ የሕገ-መንግሥቱ አዝማሚያ የቅኝ ገዢዎችን ፍላጎት ማስጠበቅ መሆኑ ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለው አይካድም" ብለዋል።

አፍሪካውያን ከራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የራሳቸውን ሕገ-መንግሥት ማዘጋጀት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።

ሌላኛው የሕግ ባለሙያ ደበበ ኃይለሚካዔል በበኩላቸው፤ የሕገ-መንግሥቱን ይዘት ሳይሆን አፈጻጸሙን እንደ ዋነኛ ችግር ያነሳሉ።

የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አባል የሆኑት የሕግ ባለሙያው አቶ ደበበ፤ "አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት ጥሩ የሆነ ሕገ መንግሥት ቢኖራቸውም፣ ሕገ-መንግሥቱን አክብሮ ተጠያቂነትን በማምጣት ተግባራዊ በማድረግ በኩል ግን ክፍተት አለባቸው" የሚል ሐሳብ ሰጥተዋል።

ባለሙያው አክለውም በአሁኑ ወቅት በርካታ የአፍሪካ ሀገራት በመንግሥት ግልበጣና በጦርነት ውስጥ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ "የአፍሪካ ሀገራት በአፍሪካ ያለውን ድህነት፣ ጦርነት እና አለመረጋጋት ለማስቆም እንዲሁም ሕገ-መንግሥታቸው በአግባቡ ተፈጻሚ እንዲሆን፤ በአፍሪካዊ አስተሳሰብ እንዲሻሻልም ለማድረግ በጋራ መምከርና መሥራት አለባቸው" ብለዋል።

26 የአፍሪካ ሕገ መንግሥታዊ ፍ/ቤቶች እና መሰል ተቋማት በተሳተፉበት በዚህ መድረክ፤ የ22 አባል ሀገራት ሕገ-መንግሥታዊ ፍ/ቤቶች እና መሰል ተቋማት ፕሬዝዳንቶች እና ሌሎች ልዑካን ቡድኖች እንዲሁም፤ ከራሽያ እና ከቱርክ የታዛቢ ሀገራቱ ተወካዮች፣ ከስፔን፣ ከጀርመን፣ ከቻይና፣ ከላቲቪያ እና ከሌሎች ሀገራት የዘርፉ ምሁራን ተሳትፈዋል።


#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ