ሐምሌ 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጣና ሐይቅን እና በዙሪያው ያሉ ደሴቶችን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በቀጣይ ዓመት እንደሚመዘገብ ለአሐዱ አስታውቋል።

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ኃላፊ አባይ መንግስቴ ሐይቁ እስካሁን በብዝሃ ሕይወት ሀብቱ ስብጥር በዩኒስኮ ተመዝግቦ መቆየቱን አስታውሰው፤ "በዓለም አቀፍ ደረጃ ሦስተኛ የተፈጥሮ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ የቅድመ ዝግጅት ሥራ አጠናቀናል" ሲሉ ገልጸዋል።

"ይህ ሀብት በዩኔስኮ ሲመዘገብ ከሰሜን ብሔራዊ ፓርክ ቀጥሎ ሁለተኛ የተፈጥሮ ሀብት ሆኖ በክልሉ ይመዘገባል" ሲሉም አስረድተዋል፡፡

Post image

በአገር አቀፍ ደረጃ ጂኦ ፓርክ እና ጂኦ ቱሪዝም ጋር በተያያዘ ለጂኦ ፓርክ የሚሆኑ ቦታዎች በክልሉ የሚገኙ መዳረሻ ቦታዎች የመለየት ሥራ እንደ አዲስ እየተሰራ መሆኑንም ምክትል ቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል።

ክልሉ በዚህ ዓመት 5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ከቱሪዝም ገቢ ማግኘት መቻሉን አስታውቋል።

በክልሉ ከሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች አንፃር በቂ አለመሆኑን ያነሱት ኃላፊው፤ "ክልሉ የሚገኝበት ነባራዊ ሁኔታ የተሻለ ገቢ እንዳይመዘገብ አድርጎል" ሲሉ ገልጸዋል።

Post image

በአጠቃላይ በዚህ ዓመት 9 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሰዎች ለጉብኝት ወደ ክልሉ መግባታቸውንም ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ጣና ሐይቅ በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በአማራ ክልል የሚገኝ ሐይቅ ሲሆን፤ በስፋቱም በኢትዮጵያ ቀዳሚ ሐይቅ ነው።

በሐይቁ ውስጥ በቋጥኝ እና በደን የተሸፈኑ ከ37 በላይ ደሴቶች የሚገኙም ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ 20ዎቹ ታሪካዊ ገዳማትን እና አድባራትን ይዘዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ