ሐምሌ 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በ2017 በጀት ዓመት ውስጥ ለማህበራዊ ችግር ተጋላጭ ናቸው ተብለው የተለዩ 244 የሚሆኑ አካል ጉዳተኞች የሙያ ስልጠና መውሰዳቸውንና ከስልጠና በኋላ የሚሰሩበት ግብዓት ድጋፍ እንደተደረገላቸው የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ሕጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ለአሐዱ አስታውቋል።
የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ቆንጅት ደበላ፤ አካል ጉዳተኞችን ከማገዝና ከመደገፍ አንፃር በርካታ ሥራዎች እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
ከስልጠና ባለፈ ወደተግባር የሚሰማሩበትን ዕድል የማመቻቸት ሥራ ከሦስት ዓመት በፊት የተጀመረና በ35 አካል ጉዳተኞች ብቻ ተጀምሮ በየዓመቱ ቁጥራቸው እየጨመረ ስለመምጣቱ አንስተዋል።
በ2017 በጀት ዓመት በተለያዩ ሙያዎች ስልጠና ወስደውና የሙያ ብቃታቸው (COC) በብቃት አረጋጋጭ ተቋም ተረጋግጦ ለሥራቸው የሚያገለግላቸውን ግብአት ቢሮው ማስረኩን ተናግረዋል።
በቢሮው የአካል ጉዳተኞችና የአረጋውያን የቤተሰብ ማስተባበሪያና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ህይወት በቀለ በበኩላቸው፤ 153 የሚሆኑት በልብስ ስፌት እና 26ቱ ደግሞ በቆዳ ስፌት ማሽን ከ5 እስከ 6 ወር መሰልጠናቸውን አንስተው የሚሰሩበት ማሽን መሰጠቱን ገልጸዋል።
ቢሮው በካፒታል በጀት ይዞ ሥራውን እንደሚያከናውን ገልጸው፤ በ2017 በጀት ዓመት 244 ለሚሆኑ ዜጎች ለመስሪያ እቃ ብቻ ወደ 8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ማውጣቱን አስታውቀዋል።
ይህ ሥራ ሲሰራም ለሁሉም የአካል ጉዳተኞች ሳይሆን ለማህበራዊ ችግር ተጋላጭ ለሆኑ፣ የመማር አቅም ለሌላቸው እና በተለያየ ምክንያት ትምህርታቸውን ላቋረጡ ዜጎች ሲሆን፤ በአጫጭር ስልጠናዎች የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ሕይወት የሚያሻሽሉበትን ስርዓት ለመዘርጋት ያለመ ስለመሆኑም ለአሐዱ ተናግረዋል።
ይህ ለማህበራዊ ችግር ተጋላጭ ናቸው ተብለው ለተለዩ አካል ጉዳተኞች የሚደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ቆንጅት ደበላ አስታውቀዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በመዲናዋ ለማህበራዊ ችግር ተጋላጭ የሆኑ 244 አካል ጉዳተኞች የሙያ ስልጠና መውሰዳቸው ተገለጸ
