ሐምሌ 1/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያዊን፤ ኮንትራክተሮች፣ የሆቴል ባለሙያዎችና የተለያዩ ሙያተኞች በደቡብ ሱዳን ተሰማርተው እየሰሩ እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህን የስራ ስምሪት ሕጋዊ ለማድረግ ስምምነት እንደምታደርግ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታውቋል።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል እንደተናገሩት ከሆነ፤ ኢትዮጵያዊያን ወደ የትኛውም ጎረቤት ሀገራት ጋር ለሥራ ስምሪት ሲሄዱ ሕጋዊ የሆነ ሥራ እንዲሰሩ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል፡፡

አክለውም ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት በዚህ ሳምንት እንደምታደርግም ጠቁመዋል።

ሚኒስትሯ ይህንን ንግግር ያደረጉት በትላንትናው ዕለት ሦስተኛው የአፍሪካ ፎረም የሥራ እድል ፈጠራ ላይ በአድዋ ሙዝየም ተገኝተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

መንግሥት በሀገር ውስጥ ከሚገኙ ከግሉ ዝርፍ እና መንግስታዊ ካልሆኑ አለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ያለውን ትስስር በማጠናከር የሥራ አጥ ቁጥርን ለመቀነስ ልዩ ትኩረት አድርጓ እየሰራ እንደሚገኝም የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ገልጸዋል።

"በዘንድሮው ዓመት ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል" ሲሉ የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ ይህም ለዜጎች የሥራ ዕድል የመፍጠሩ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በደረጄ መንግስቱ
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ