ጥቅምት 17/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በነገው ዕለት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ይሰጣሉ፡፡
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ጥቅምት 18 ቀን 2018 ዓ.ም ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ይካሄዳል፡፡
በመደበኛ ስብሰባው ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ መስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ም/ቤቶች የጋራ ስብሰባ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ ከም/ቤቱ አባላት በሚቀርቡ ጥያቄዎች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽና ማብራሪያ ይሰጣሉ፡፡

ምክር ቤቱም የመንግሥትን አቋም በማዳመጥ የድጋፍ ሞሽኑን ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በዚህም የምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ ላይ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተጠሪዎች፣ የሐይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ ተጠሪዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ አሐዱ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የስብሰባው ሙሉ ሒደት በቀጥታ ሥርጭት ለሕዝብ የሚተላለፍ መሆኑንም ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ