ጥቅምት 17/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የተንቀሳቃሽ ስልክ ሲም ካርዶችን እና ተያያዥ የቴሌኮም አገልግሎቶችን ከ'ፋይዳ' ብሔራዊ መታወቂያ ጋር በማስተሳሰር፣ ተገልጋዮች ከቴሌብር የሚወስዱትን ብድር በአግባቡ እንዲመልሱ የሚያስገድድ አሠራር ሊተገበር እንደሆነ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ለአሐዱ አስታውቋል።

አዲሱ አሰራር የቴሌብር ብድራቸውን ላለመክፈል ሲም ካርድ የሚጥሉ፣ ሲምካርድ የሚቀይሩ እና የቴሌብር አገልግሎቶችን የሚያቋርጡ አንዳንድ ግለሰቦችን ሕገ-ወጥ ተግባር እንደሚያስቆም ታምኖበታል፡፡

የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የባለድርሻ አካላትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳሚናስ ሰይፉ ለአሐዱ እንደገለጹት፤ ፕሮግራሙ በተያዘው በጀት ዓመት ከሌሎች አገልግሎቶች በተጨማሪ በቴሌኮም ዘርፍ ላይ በስፋት ይሠራል።

አቶ ሳሚናስ የቴሌኮም ዘርፍ ላይ እየተሰጠ ያለው ብድር አነስተኛ መሆኑን አንስተው፤ አገልግሎቱን ከፋይዳ ጋር ማያያዝ አሁን ካለው አቅም በላይ እንዲጨምር እንደሚያግዘው ተናግረዋል።

ይህ አዲስ አሠራር የብድር አገልግሎቱን በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገባ ከማድረጉም በተጨማሪ፤ እንደ ሞባይል ዳታ እና የአየር ሰዓት ለመሳሰሉ አገልግሎቶች ሊሰጥ የታሰበውን አዳዲስ የብድር አገልግሎት አይነቶች ለማስተዋወቅ እንደሚረዳ አብራርተዋል።

የቴሌብር ብድር ከሲምካርድ እና ከፋይዳ መታወቂያ ጋር መተሳሰሩ ግለሰቦች በተለያየ ማንነት ከኢትዮ-ቴሌኮም በሚያወጧቸው ሲምካርዶች የሚፈጽሙትን ማጭበርበር ያስቀራል ተብሏል።

በተጨማሪም ፋይዳ እና ባንኮች በፈጠሩት የቀደመ ትስስር አማካኝነት ብድራቸውን ለመክፈል ፈቃደኛ ያልሆኑ ተበዳሪዎችን ለማስገደድ ያግዛል እንዲሁም ተበድረው የሚጠፉትን ከፖሊስ ጋር በመተባበር ለመያዝ ያስችላል የተባለ ሲሆን፤ ነገር ግን አሠራሩ በትክክል መቼ እንደሚጀመር አልተገለጸም፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ