ጥቅምት 17/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው የኮሪደር ልማት ምክንያት ሙሉ ለሙሉ የፈረሱ እና በከፊል የተጎዱ 13 የነዳጅ ማደያዎች በአዲስ ቦታ ተገንብተው በቅርብ ጊዜ ሥራ እንደሚጀምሩ ነዳጅ እና ኢነርጂ ባለሥልጣን ለአሐዱ አስታውቋል።

ባለሥልጣኑ "የተገንቡት ማደያዎች ወደ ሥራ መግባት የሚያስችላቸውን ፈቃድ ሰጥቻለሁ" ብሏል።

የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ደስታው መኮንን (ዶ/ር)፤ "በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ሲሰሩ የነበሩ እና በኮሪደር ልማት ምክንያት የፈረሱት ማደያዎች ተገቢ ቦታ ተመቻችቶላቸው በድጋሚ እንዲገነቡ ተደርጓል" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

Post image

የማደያዎቹ በድጋሚ መገንባት በልማቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማት ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው የመመለስ ጥረት አካል መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በክልል ከተሞችም ተመሳሳይ የኮሪደር ልማት ጋር በተያያዘ በከፊልና ሙሉ ለሙሉ የፈረሱ የነዳጅ ማደያዎችን በማደስ ወደ ሥራ እንዲገቡ ፈቃድ መሰጠቱን ተናግረዋል።

በከተሞች መካከል ያሉ የነዳጅ ማደያዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን እንደ ችግር ያነሱም ሲሆን፤ ችግሩን የፈጠረው "በሀገሪቱ ያሉ ነዳጅ ማደያዎች በጥናት ላይ ተመስርተው አለመገንባታቸው ነው" ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ማደያዎች የሚገነቡት ከከተማ አስተዳደሩ በሚሰጥ ፈቃድ መሆኑን አስታውሰው፤ "ባለሥልጣኑ ይሄንን ችግር ለመፍታት በየትኛው አካባቢ ምን ያህል የነዳጅ ማደያ ያስፈልጋል የሚለውን በማጥናት የጥናቱ ውጤት እና ምክረ-ሐሳቦቹን ለጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ልኳል" ብለዋል።

በጥናት የተደገፈው አሰራር ተግባራዊ ሲደረግ ከፍተኛ ወረፋ እና መጨናነቅ ያለባቸውን እና የነዳጅ ማደያ እጥረት ያለባቸውን አካባቢዎች ችግር ያቃልላል የሚል እምነት እንዳላቸውም የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ተናግረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ