መስከረም 16/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በ80ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንግግር ለማድረግ ወደ መድረክ በወጡበት ወቅት፤ የበርካታ ሀገራት ልዑካኖች በኒውዮርክ ከሚገኘው የድርጅቱ የስብሰባ አዳራሽ ጠቅላላ ጉባኤን ለቀው ወጥተዋል።

እ.ኤ.አ ጥቅምት 7 በሃማስ መሪነት የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ላይ እያደረሰች ባለችው መጠነ ሰፊ ጥቃት ምክንያት ዓለም አቀፍ ተቃውሞ እየጨመባት መምጣቱ ይታወቃል፡፡

ይህም እስራኤል በጋዛ ላይ በተከታታይ እያደረሰችው ያለው ጥቃት፤ በበርካታ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ሀገራት ዘንድ ተቃውሞ ደርሶበታል።

በዛሬው ዕለትም የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በድርጅቱ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ንግግር ለማድረግ ወደ መድረክ በመውጣት ላይ ሳሉ፤ በርካታ የአባል ሀገራት ልዑካኖች ንግግራቸውን ላለመስማት ጉባኤውን አቋርጠው ከአዳራሽ ወጥተዋል፡፡

Post image

በዚህም ወቅት ልዑካኑን የሚደግፍ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ኒታንያሁን የሚቃወም የጅምላ ድምጽ እና ጭብጨባ በአዳራሹ ተሰምቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ እስራኤል በኢራን እና በመካከለኛው ምስራቅ ባሉ አጋሮቿ ላይ የምታደርገውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ አንስተዋል፡፡

በዚህም "ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ትናንትን ጨምሮ የሁቲዎችን እና ከፍተኛውን የሃማስ የሽብር መሳሪያዎች ጨፍልፈናል። ሂዝቦላን አካለ ስንኩላን አደረግን፣ አመራሮቹን እና አብዛኛው የጦር መሳሪያ ከግምጃ ቤቱን አውጥተናል" ብለዋል።

በዚህ ባለፈው ዓመት ያደረግነው፣ በዚህ አስር ዓመታት ውስጥ የተከማቹ የኢራንን የአቶሚክ መሳሪያዎች እና የባለስቲክ ሚሳኤሎች ፕሮግራሞችን ማውደም ነው" ሲሉ አክለዋል።

Post image

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ቀደም ሲል በሰጠው መግለጫ “የሲቪል አካላት ከእስራኤል መከላከያ ሰራዊት (አይ.ዲ.ኤፍ) ጋር በመተባበር፤ በእስራኤል ጋዛ ድንበር ላይ ብቻ በጭነት መኪኖች ላይ ድምጽ ማጉያ እንዲያስቀምጡ መመሪያ ሰጥቷቸዋል” ማለቱ ይታወሳል፡፡

ኔታንያሁ ይህን ታሳቢ ያደረገ መልዕክት በጋዛ ለሚገኙ ታጋቾች በቀጥታ በመጀመሪያ በዕብራይስጥ ከዚያም በእንግሊዘኛ አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም፤ "ውድ ታጋቾቻችን በጋዛ ከዚህ ማይክሮፎን ጋር የተያያዙ ግዙፍ ድምጽ ማጉያዎችን ከባችሁ መልእክቴን እንደምትሰሙ አስባለሁ" ብለዋል።

“ጀግኖቻችን ይህ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ነው፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በቀጥታ፤ እናንተን ለአንድ ሰከንድ እንኳን አልረሳችሁም። የእስራኤል ሕዝብ ከእናንተ ጋር ነው፣ አንደናቀፍም እና ሁላችሁንም ወደ ቤት እስክናመጣችሁ ድረስ አናርፍም" ብለዋል፡፡

"ስለዚህ ለቀሪዎቹ የሃማስ መሪዎች እና ለታጋቾቻችን እስረኞች አሁን እላለሁ፤ ትጥቃችሁን አኑሩ። ህዝቤን ልቀቅ። ታጋቾቹን ሁሉ፣ 48ቱንም ነፃ አውጡ" ብለዋል ኔታንያሁ። "ሃማስ አሁን ይህን ቢያደርግ በሕይወት ይኖራል። ካላደረገ ግን እስራኤል ያሳድደዋል" ሲሉም አሳስበዋል፡፡

አክለውም፤ ሃማስን ከጋዛ የማጥፋት ሥራውን እንደሚያጠናቅቁ በጠቅላላ ጉባኤው ንግግራቸው ላይ ቃል ገብተዋል።

"የመጨረሻዎቹ የሃማስ ቅሪቶች በጋዛ ከተማ ውስጥ ተከማችተዋል። የእ.ኤ.አ. ጥቅምት 7 የፈጸሙትን ጭካኔዎች ደጋግመው ለመድገም ቃል ገብተዋል፣ ምንም ያህል ሀይላቸው ቢቀንስም" ብለዋል።

"ለዚህም ነው እስራኤል ሥራውን መጨረስ ያለባት። ለዚህም ነው በተቻለ ፍጥነት መስራት የምንፈልገው።" ሲሉም ለጉባኤው ተናግረዋል፡፡

ኔታንያሁ "አብዛኛው ዓለም ከአሁን በኋላ ጥቅምት 7ን አያስታውስም ነገርግን እኛ እናስታውሳለን" ያሉም ሲሆን፤ በለበሱት የሱፍ ጃኬት ላይ የኪው አር ኮድ (QR code) ከጥቅምት 7 የጭካኔ ድረ-ገጽ ጋር የሚያገናኝ መሆኑን ተናግረዋል።

Post image

አክለውም “እ.ኤ.አ ጥቅምት 7፣ ሃማስ ከጅምላ ጭፍጨፋው በኋላ በአይሁዶች ላይ የከፋ ጥቃት ፈጽሟል። 1 ሺሕ 200 ንፁሃን ዜጎችን፣ ከ40 በላይ አሜሪካውያን እና እዚህ የተወከሉ በደርዘን የሚቆጠሩ ሀገራት ዜጎችን ጨፍጭፏል" ብለዋል፡፡

ኔታንያሁ ሰኞ ዕለት ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ይገናኛሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ተደራዳሪዎች በጋዛ ያለውን ጦርነት ለማስቆም እና ታጋቾችን ለመመለስ ስምምነት ላይ ለመድረስ "በጣም ቅርብ ናቸው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ለጋዜጠኞች መናገራቸው ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡

እስራኤል እ.ኤ.አ ከጥቅምት 7 ቀን 2023 ጀምሮ በጋዛ መጠነ ሰፊ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈፀመች ሲሆን፤ ከ65 ሺሕ 400 በላይ ፍልስጤማውያንን በጋዛ ሕይወታቸው ሲያልፍ፤ በርካታ ሴቶች እና ሕጻናት በጥቃቶቹ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ