መስከረም 16/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) ‎በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በጉራጌ ዞን በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል የመስቀል በዓል አንዱ ሲሆን፤ በዚህም በዓሉን ምክንያት አድርገው ግብዓቶች እና ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሬ በሚያደረጉት ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ለአሐዱ አስታውቋል።

‎በክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሀመድ ኑርሳል ለአሐዱ እንደገለፁት፤ በክልሉ 89 የነዳጅ ማደያዎች ያሉ ሲሆን፤ የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ ኮማንድ ፖስት በማቋቋም ጥብቅ ክትትል እየተደረገ ነው፡፡

በዚህም የዋጋ ጭማሪ እና ሌሎች ሕገ-ወጥ ተግባሮችን ሲፈጽሙ የተገኙ፤ 32 በሚሆኑ የነዳጅ ማደያዎች ላይ ክስ መመስረቱን ምክትል ኃላፊው ገልጸዋል።

‎በዓሉን ለማክበር ወደ ክልሉ ከተለያየ ቦታ የሚገባው ሕዝብ በርካታ በመሆኑ በነዳጅ እጥረት ምክንያት የትራንስፖርት እንቅስቃሴው እንዳይስተጓጎል ወደ 2 ሚሊዮን ሊትር የናፍጣና ከ850 ሺሕ በላይ የቢንዚን ክምችት መኖሩን አቶ ሙሀመድ ገልጸዋል።

‎ምክትል ኃላፊው በኮንትሮባንድ እና በመሰወር ተግባር ላይ በተሰማሩ ማደያዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን አንስተው፤ በክልሉ ካሉ የነዳጅ ማደያዎች መካከል በሁለት ወረዳዎች ምንም አይነት ማደያ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን የነዳጅ እጥረት እንዳይፈጠር በችርቻሮ የሚሸጡ ነጋዴዎች በበቂ ሁኔታ እንዲያቀርቡ ተደርጓል ብለዋል።

‎በክልሉ የነዳጅ ስርጭቱ ሕጋዊና ጤናማ እንዲሆን እየተደረገ ያለው ቁጥጥር ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ተናግረዋል።

‎ምክትል ኃላፊው አያይዘውም ያልተገባ የዋጋ ጭማሬ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ክትትል ተደርጎ በመጋበዝና ሱቆች ላይ እርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ