ሕዳር 23/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ ግጭቶች፣ የኢኮኖሚ አለመረጋጋት እና የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተሉት ቀውስ ሠራተኞች ሥራቸውን በአግባቡ እንዳያከናውኑና ምቹ የሥራ አካባቢ እንዳይኖራቸው ፈተና እየሆኑ መምጣታቸውን ዓለም አቀፉ የሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ITUC) አስታወቀ።
ይህ መግለጫ የተሰጠው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (CETU) ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ባዘጋጁት 37ኛው የዓለም አቀፉ የሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ነው።

ስብሰባው የዓለም አቀፉ ኮንፌዴሬሽን፣ የቻይና የሠራተኞች ኮንፌዴሬሽን፣ ከሰሃራ በታችና የአፍሪካ ቀንድ ሠራተኞች ኮንፌዴሬሽን እንዲሁም፤ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ዛሬ ሕዳር 23 ቀን 2018 ተካሂዷል።
የዓለም አቀፉ የሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ ሉክ ትሪያንግል በስብሰባው ላይ እንደተናገሩት፤ ዓለም አቀፍ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ሠራተኞችን እየፈተኑ ነው።

ከዚህ ባሻገር፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የእኩል ተጠቃሚነት አለመኖር ሌሎች ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቁመው፤ ዓለም አቀፉ ኮንፌዴሬሽን ችግሮችን ለመፍታት እንደሚሠራ ገልጸዋል።
በተመሳሳይም የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ፤ በዓለም ዙሪያ ያሉ ሠራተኞች የዝቅተኛ ደመወዝ ክፍያ፣ ሥራ አጥነት፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና ግጭቶችን ጨምሮ በርካታ ችግሮችን እየተጋፈጡ እንደሆነ አብራርተዋል። በመሆኑም፤ በየትኛውም ቦታ የሚገኙ ሠራተኞች መብታቸው ሊጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ካሳሁን የዛሬው ጉባኤ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደተካሄደ ገልጸዋል፡፡ ኮንፌዴሬሽኑ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለማስገኘትና ለኢትዮጵያ ሠራተኞችም ትልቅ ዕድል እንደሆነም ተናግረዋል።
አክለውም ኢትዮጵያ የሠራተኞችን ድምፅ ለመሆንና መብትና ጥቅማቸውን ለማስከበር እንደተቋቋመች ገልጸው፤ አሁንም ከአጋር አካላት ጋር በመሆን የሠራተኞችን መብት ለማስከበር እንደሚሠሩ አስታውቀዋል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያም ለሠራተኞች ተግዳሮት የሆኑ ጉዳዮችን ለመፍታት መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ የሠራተኞች ማኅበራት ይህንን ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

በተጨማሪም፣ በአሠሪ፣ በሠራተኛ ማኅበራትና በመንግሥት መካከል ያለው ግንኙነት የተጠናከረ መሆን እንዳለበት አክለዋል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በመጠበቅ ለሠራተኞች መብት፣ እኩልነትና አካታችነት እየሠራች እንደምትገኝ የገለጹት አቶ አደም፤ ከዓለም አቀፉ የሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ጎን እንደምትቆም አስታውቀዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ