ሕዳር 23/2018 (አሐዱ ሬዲዮ) የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሠራተኞችን ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል የሚወስን ቦርድ እንዲቋቋም የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራ ማጠናቀቁን ለአሐዱ ሬዲዮ አስታውቋል።
አዲስ የሚቋቋመው ቦርድ 'የሠራተኞችን የዝቅተኛ ደመወዝ ይወሰን' ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ከመንግሥት በተጨማሪ የሠራተኛና የአሠሪ ኮንፌዴሬሽኖች የሚሳተፉበት ይሆናል ተብሏል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ዳንኤል ተሬሳ፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቦርዱ እንዲቋቋም የሚያስችል መመሪያ እንዳዘጋጀ ለአሐዱ ተናግረዋል።
ቦርዱ የሠራተኞችን የዝቅተኛ ደመወዝ ጥያቄዎች ለመፍታት እንደተቋቋመና በመንግሥት፣ በተቀጣሪ ሠራተኞች እና በአሠሪዎች ትብብር እንደሚቋቋም አብራርተዋል።

ሚኒስቴር ዴኤታው አክለውም፤ የሚቋቋመው ቦርድ ጥናት ላይ የተመሠረተ ሥራዎችን በማከናወን የሠራተኞችን ጥቅም እና ችግር ይፈታል፤ ቦርዱ የሠራተኞችን መብትና ክብራቸውን ተጠብቆ እንዲሠሩ ከማስቻል ባሻገር በሀገሪቱ ያለውን ከፍተኛ የሥራ-አጥ ቁጥር ለመቅረፍ ለግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠርም ያግዛል ሲሉ አብራርተዋል።
በተጨማሪም በሀገሪቱ ኢንዱስትሪው እየተስፋፋ ሲመጣ ከጥቅሙ ባሻገር አብረው የሚመጡ ችግሮችን በአንድነት ለመፍታትና የሠራተኞችን መብት ለማስጠበቅ ቦርዱ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።
የዓለም አቀፍ የሠራተኞች ኮንፌዴሬሽን 32ኛው ጉባኤ ወደ አፍሪካ የመጣው ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑንና ጉባኤው በአዲስ አበባ መካሄድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አመልክተዋል።
የኮንፌዴሬሽን አባላት ከተለያዩ ሀገራት መምጣታቸው ለሀገሪቱ ለውጥ እና የተሻሻለው አዲሱ የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ ተጠቃሽ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ