የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለመጨረሻወ ዋና ጉባኤ ጥቂት ወራት እንደቀሩት እየገለጸ ነው።

ይሁን እንጂ ይህንን ጉባኤ እውን ለማድረግ ወደ ኋላ የሚጎትቱ ጉዳዮች መኖራቸው ይገለፃል።

በዋናነትም ኮሚሽኑ የትግራይ ክልል አጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ አለመስራቱ ዋናዉ ጉባኤ እንዲዘገይ ጭምር ማድረጉን ኮሚሽኑ እያነሳ ይገኛል።

በዛሬው ዕለትም ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ ከሐይማኖት ተቋማትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቾች ጋር ውይይት አድርጓል። ውይይቱም "የላቀ ተሳትፎ ለሀገራዊ ምክክር ውጤታማነት" የሚል መድረክ ተዘጋጅቶ ወይይት ተከናውኗል።

ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር)፤ ኮሚሽኑ ከብዙ ሂደት በኋላ የምምክሩ ጉባኤውን የሚመክርባቸውን አጀንዳዎች መቅረፅ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

Post image

በተጨማሪም ምክክር ጉባኤውን ለመጥራት ጫፍ ላይ መድረሱን የገለጹ ሲሆን፤ "ይሁን እንጂ ወደዚህ ተግባር ለመግባት መከናወን ያለባቸው ወሳኝ ተግባርተ አሉ" ሲሉ ንግግራቸውን ቀጥለዋል፡፡

በዋናነትም ትግራይ ክልል እንደሌሎች ክልልች አጀንዳዎችን እንዲሰብሰብ ወሳኙ ቀሪ ሥራ መሆኑን ዋና ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ ደግሞ ከምከክሩ ሂደት የወጡ ፖለቲካ ፓርቲዎች እና የታጣቁ ኃይሎች ወደ ምክክሩ አለመገባትም ከቀሪ ሥራዎች መካከል የሚጠቀሱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቆይታ ጊዜው የተራዘመለት ቢሆንም፤ እሱም ወደ መጠናቀቁ ተቃርቧል፡፡

በመሆኑም በቀሩት ጥቂት ወራት ውስጥ እነዚህን ወሳኝ የተባሉ ሥራዎችን ያጠናቅቃል ወይ? የሚለውም የብዙሃኑ ጥያቄ ነው፡፡

የትግራይ ክልል አጀንዳ ማሰባሰብ መዘግየት ለዋናው ጉባኤ እንዲዘገይ ያደረገ መሆኑን፤ ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ አንስተዋል።

"የተለያዩ ውይይቶች የተደረጉ ቢሆንም፤ ዉጤታማ የሆነ ሥራ መስራት አልተቻለም" ሲሉም ኮሚሽነሯ ተናግረዋል።

Post image

አክለውም፤ "በትግራይ በኩል መቼ አጀንዳ ማሰባሰብ ሥራውን መስራት እንደምንችል አልተገለጸልንም" ብለዋል፡፡ ይህንንም የገለጹት ኮሚሽኑ በምክክሩ ሂደት ያጋጠሙ ዋና ዋና ተግዳሮችን በገለጹበት ወቅት ነው።

ሌላው የፖለቲካ ፖርቲዎች የሚያነሷቸዉ ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ ሁሉም ፖርቲዎች መሳተፍ አለመቻላቸዉ መሆኑን ኮሚሽነሯ ገልጸዋል።

በምክክሩ ሲሳተፉ የቆዩ እንዲሁም ከመጀመሪያው ጀምሮ ከኮሚሽኑ እራሳቸዉን ያገለሉ ፖርቲዎች ወደ ምክክሩ አለመመለስ ለሥራቸው ዋነኛ ተግዳሮት ስለመሆኑ አንስተዋል።

ሌላዉ ኮሚሽኑ ከታጣቂዎች አጀንዳ ለመሰብሰብ የሞከረው ሙከራ ሊሳካ አለመቻሉንም ኮሚሽነር ሂሩት ተናግረዋል።"ጥሪውን ተቀብሎ ምላሽ የሰጠ ምንም አይነት የታጣቂ ቡድን የለም" ያሉም ሲሆን፤ ይህም ከኮሚሽኑ ተግዳሮቶች አንዱ ነዉ ብለዋል።

በተጨማሪም በሕብረተሰቡ ዘንድ ስለ ምክክር ኮሚሽን በበቂ ሁኔታ ግንዛቤ አለመኖሩንም ኮሚሽኑን እየፈተነ ያለው ጉዳይ መካከል መሆኑን አንስተዋል።

ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን የግንዛቤ ሥራ ሲሰሩ መቆየታቸውንም ተናግረዋል።

Post image

የትግራይ ክልል የአጀንደ ማሰባሰብ ሥራውን አለማጠናቀቃቸው ጊዜ እንዲያቃጥሉ ስለማድረጉ ያነሱም ሲሆን፤ "ይህም ለሥራው ከፍተኛ ተግዳሮት ሆኖብናል" ብለዋል።
በመሆኑም "የሐይማኖት ተቋማት እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እርዳታችሁ ያስፈልጋል" ሲሉ አስገንዝበዋል።

ከተነሱት ተግዳሮቶች በመቀጠል ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንዲሁም፤ ከሐይማኖት ተቆማት ጠንከር ያሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል።

በመጀመሪያዉ ከተነሱ ሀሳቦች መካከልም "ወደ ምክክሩ ያልመጡ አካላትን የትግራይ ክልል ጨምሮ እሰከ መቼ ነው የሚጠበቁት?" የሚል ጥያቄ ቀርቧል።
"የቀሩት አካላትስ የማይመጡ ከሆነ እነሱን ጥለን ነው ወይ ጉባኤ የምናካሂደዉ?" የሚል ጥያቄም ከተሳታፊዎች ተነስቷል።

Post image

በተጨማሪም "ምርጫ ለማድረግ እየተነሳን ባልንበት ሁኔታ ጉባኤ ማድረግ አይጋጭም ወይ? ምክክሩ ይቀድማል ወይስ ምርጫዉ ይቀድማል?" የሚሉ ጥያቄች ቀርበዋል።

ሌላው በዛሬው ጉባኤ ላይ ተሳታፊ የነበሩ የሐይማኖት ተቋማት በርከት ያሉ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፤ ከእነዚህ መካከልም ከእስልምና እንዲሁም ከኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ወክለው ተገኙ የሐይማኖት አባቶች ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡

Post image

በዋናነትም አሁን በምክክሩ እየተሳተፉ የማይገኙ የትግራይ ክልል እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ በአቋማቸው የሚጸኑ ከሆኑ ኮሚሽኑ እንደ ሁለተኛ ምርጫ የያዘው ሀሳብ ስለመኖሩ ጠይቀዋል፡፡

ሌላው "ፓርቲዎች ለምን ከኮሚሽኑ ለመራቅ ወሰኑ?" የሚል እና አንድ ጊዜ ሞቅ አንደ ጊዜ ቀዝቀዝ የሚለው የኮሚሽኑ የንቅናቄ ሥራ ላይ ጥያቄ አንስተዋል፡፡

ኮሚሽኑ በዛሬው የምክክር መድረክ ላይም በተነሱ ሀሳቦች ላይ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች በተለያዩ ምላሾችና ማብራሪያዎችን ሰጥውበታል፡፡

ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ በሰጡት ምላሽ፤ "በቀረን የጊዜ ገደብ ውስጥ ቀሪ ሥራዎቻችን የመጨረስ ሁኔታ ይኖራል የሚል ዕምነት የለንም" ሲሉ ተናግረዋል።

ነገር ግን ኮሚሽኑ በቀሩት ወራት ውስጥም ሥራውን ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ የገለጹ ሲሆን፤ ነገሮች ከተስተካከሉ በየትኛውም መንገድ ቢሆን የትግራይ ክልል ውክልና እንዲያገኝ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡

"ከፖርቲዎች ጋር በተያያዘ በኮሚሽነሮች ላይ የሚነሳው የተዓማኒነት ጉዳይ በሥራችን ብቻ መመዘን ይኖርብናል" ሲሉም አስረድተዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባዬ ኡጋቶ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ከምርጫ ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጥያቄ "ምርጫ ውድደር ነው" ብለዋል፡፡ "አንዱ ሌላውን ጥሎ ለማለፍ የሚደርግ ነው" ያሉ ሲሆን፤ "ምክክር ደግሞ ተነጋግሮ ትውልድ የመገንባት ሥራ ነው" ሲሉ አክለው ገልጸዋል፡፡

Post image

በመሆኑም ሕጉን ተከትሎ ሥራውን ማጠናቀቅ የሚቻል ከሆን ከምርጫ በኃላ የሚደረግ ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡ "ነገር ግን 'ምርጫ ስላለ ምክክር አይደረግም' ተብሎ የሚታሰብበት ሁኔታ የለም" በማለት ዶክተር አምባዬ ገልጸዋል፡፡

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋናውን ጉባኤ ለማድረግ ዝግጅት እና የአጀንዳ ልየታ እየሰራ ቢሆንም፤ የትግራይ ክልል አጀንዳ አለመሰብሰብ ልሰራው እንቅፋት እንደሆነበት ገልጿል፡፡

Post image

በመሆኑም ኮሚሽኑ በቀሩት ወራት በተግዳሮት ተቀመጡትን ሥራዎቹን አጠናቆ ዋናውን ጉባኤ ለማደረግ ማለሙን ያነሳ ሲሆን፤ ነገር ግን መሳካቱን እርግጠኛ መሆን አይቻልም ተብሏል፡፡

በተለይም ደግሞ የትግራይ ክልል በምክክሩ ሂደት የማይሳት ከሆነ የተቀመጠ ወይም ወሳኔ ላይ የተደረሰ አቅጣጫ አለመኖሩም ኮሚሽኑ ከሐይማኖት ተቋማት እና ከሲቪል ማህበረሰብ ድረጅቶች ጋር በነበረው ውይይት ላይ አንስቷል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ